ቀጥታ፡

አዲሱ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ 1383/2017 "ሁሉንም ዓይነት ፕላስቲኮች" ሙሉ በሙሉ አግዷል?

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የፕላስቲክ ብክለትን በመቀነስ የአካባቢን ደህንነት ለማረጋገጥ ያለመውን አዲሱን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ 1383/2017 ወደ ትግበራ ማስገባቱ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ፣ የዚህን አዋጅ መውጣት ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ላይ ማህበረሰቡን የሚያሳስቱ መረጃዎች በስፋት እየተዘዋወሩ ይገኛሉ። በመሆኑም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተሰራጩ ያሉትን ዋና ዋና አሳሳች መረጃዎች በመለየት፤ ከአዋጁ፣ ከኃላፊዎች ማብራሪያ እና ይፋዊ መግለጫዎች ጋር በማገናዘብ መረጃ ማጣራት ተደርጓል።

የተሳሳተ መረጃ፡- "ማንኛውም ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ እንዳይመረት፣ እንዳይገባ እና እንዳይሸጥ ሙሉ በሙሉ ታግዷል"

እውነታው፡-

አዋጁ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮችን በሙሉ አልከለከለም። በህጉ መሰረት ሙሉ በሙሉ የተከለከሉት ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ "ስስ የፕላስቲክ ከረጢቶች (ፌስታል)" ብቻ ናቸው። የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፤ “ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ እንዲመረት፣ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ወይም ጥቅም ላይ እንዲውል መመሪያ ሊወስን ይችላል” ይላል። ይህም ማለት እንደየአስፈላጊነቱ የሚፈቀዱ ፕላስቲኮች አሉ።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ በሰጠው ማብራሪያ፤ የፕላስቲክ ማሸጊያ ማለት እቃዎችን ከብክለት ለመከላከል ወይንም ከሌላ ነገር ጋር እንዳይቀላቀል ለማድረግ የሚጠቅም መሆኑን ጠቅሶ፤ የምግብ፣ የባልትና ውጤቶች፣ የላውንደሪ አገልግሎት እና ሌሎች ምርቶችን ለማሸግ የሚውሉ የፕላስቲክ ማሸጊያዎች በአዋጁ የተፈቀዱ መሆናቸውን አረጋግጧል። የእነዚህ ማሸጊያዎች አወጋገድ በቀጣይ በሚወጡ መመሪያዎች የሚመራ ይሆናል። በተጨማሪም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) በሰጡት ማብራሪያ፤ አዋጁ የፕላስቲክ ምርቶችን ሙሉ ለሙሉ የሚከለክል እንዳልሆነ በግልጽ አረጋግጠዋል።

የተሳሳተ መረጃ፡- "የቁጥጥር ስራውን የሚያከናውነውና እርምጃ የሚወስደው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ብቻ ነው"

እውነታው፡-

አዋጁን የማስፈጸም የበላይ ኃላፊነት የተሰጠው ለአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና ለክልል የአካባቢ ጥበቃ ቢሮዎች መሆኑ እውነት ቢሆንም፤ የቁጥጥር ስራው ግን በባለስልጣኑ ብቻ የሚከወን አይደለም። ህጉ ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ ሲደረግ፣ በየዕለቱ ህገ-ወጥ ስስ የፕላስቲክ ከረጢቶችን በሚያመርቱ፣ በሚያስገቡ እና በሚጠቀሙ አካላት ላይ ክትትል የሚያደርጉት እና የቁጥጥር እርምጃ የሚወስዱት የፖሊስ እና የደንብ ማስከበር አካላት መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።

በመሆኑም ህዝቡ እና የንግዱ ማህበረሰብ የቁጥጥር ስራው በጸጥታና ደንብ አስከባሪ አካላት ጭምር የሚተገበር መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል።

ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሱ ያልተረጋገጡ አሳሳች መረጃዎችን ባለመቀበል የፕላስቲክ አጠቃቀምን በተመለከተ የሚወጡ መመሪያዎችን በቀጥታ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይፋዊ ገጾች እና ከታማኝ ምንጮች ብቻ እንዲወስድ ይመከራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም