የሃዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የሃዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።
በዕለቱ የሚደረገው ብቸኛ መርሐ-ግብር ሃዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡናን ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ያገናኛል።
ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች በ10ሩ አሸንፎ በአራቱ ተሸንፎ በስድስቱ አቻ ወጥቷል። በጨዋታቹ ላይ 23 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሃዋሳ ከተማ በ36 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በሊጉ ካካሄዳቸው 20 ጨዋታዎች መካከል በዘጠኙ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 24 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 10 ጎሎችን አስተናግዷል።
ሲዳማ ቡና በ37 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሃዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ አንድ አቻ ተለያይቷል። ሲዳማ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ያደረገው ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።
ሃዋሳ ከተማ የሊጉ መሪ ለመሆን፣ ሲዳማ ቡና መሪነቱን ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ፍልሚያ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የመጀመሪያ ዙር በሁለተኛ ሳምንት ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።