በወራጅ ቀጠና የሚገኙት አርባምንጭ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወሳኝ ድል አስመዘገቡ - ኢዜአ አማርኛ
በወራጅ ቀጠና የሚገኙት አርባምንጭ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወሳኝ ድል አስመዘገቡ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ማምሻውን ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ባህርዳር ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ቡጣቃ ሸመና እና ይድነቃቸው ያሲን ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበው አርባምንጭ ከተማ በ16 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል።
ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።
በሊጉ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ባህርዳር ከተማ በ27 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ፋሲል ከነማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ጃቢር ሙሉ በ40ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ግብ ፋሲል ከነማ መሪ መሆን ችሏል።
ኤፍሬም ኃይለማርያም በ68ኛው እና ጋናዊው ኮንኮኒ ሀፊዝ በ92ኛው ደቂቂ የማሸነፊያ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ21 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ በ33 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።
ዛሬ ቀን ላይ በተደረጉ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ምድረ ገነት ሽሬ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2 ለ 1፣ ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።