ተቋሙ ለደንበኞች ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሠራር ሊተገብር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተቋሙ ለደንበኞች ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሠራር ሊተገብር ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞችን በትክክል ለመለየት እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ሚና ያለው አሠራር ወደ ተግባር ሊያስገባ መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በዲጂታል መለያ ማረጋገጫ አገልግሎት ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱ ደንበኞችን በዘመናዊ እና በአስተማማኝ መንገድ ለመለየት እና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን እያገለገለ መሆኑን ጠቁመው፤ ስምምነቱ ደንበኞችን በትክክል ለመለየት እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የዲጂታል መለያ ሥርዓቱ የውስጥ አሠራሮችን ለማዘመን እና ለማጠናከር እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሔ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ደንበኞች አገልግሎት ለማግኘት በሚመጡበት ጊዜ ተመሳሳይ ቅጾችን እና መጠይቆችን በተደጋጋሚ እንዳይሞሉ ያስችላል ብለዋል፡፡
ከፋይዳ ዲጂታል መለያ ሥርዓት የሚገኘውን የተሟላ እና የተረጋገጠ መረጃ በመጠቀም ፈጣን እና አስተማማኝ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም አስረድተዋል።
ይህ ስምምነት ከደንበኞች ባሻገር የአገልግሎቱን ሠራተኞች መረጃ በትክክል ለማወቅ እና የሰው ኃብት አሥተዳደርን ለማጠናከር እንደሚረዳም ነው የተገለጸው።