ቀጥታ፡

በምርጫው የሀሳብ ልዕልና እንዲያሸንፍ ስልጡን የፖለቲካ ባህል እንከተላለን - ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

ጎንደር፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ በጠቅላላ ምርጫው የሀሳብ ልዕልና እንዲያሸንፍ ስልጡን የፖለቲካ ባህል በመከተል የድርሻቸውን እንደሚወጡ በጎንደርና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሀሳብ የበላይነት የሚያሸንፍበት እንዲሆን የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንደሚከተሉም ተናግረዋል።
 
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/የጎንደር ቅርንጫፍ ተወካይ ዝናወርቅ ታደለ እንዳሉት፣ ፓርቲያቸው ትብብርና ፉክክርን መርህ ያደረገ የምርጫ ውድድር ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቅቋል።
 
የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል በማራመድና በሃሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ ምርጫ በማካሄድ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ለይ አሻራ እንደሚያኖሩ ገልጸዋል።
 
በአሁኑ ወቅትም በጠቅላላ ምርጫው በንቃት ለመሳተፍ የምርጫ ምልክታቸውንና ማኒፌስቷቸውን ለሕዝብ እያስተዋወቁ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት ተገኑ ደረጀ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡን አክብሮ ለውድድር እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ሀገራዊ ጥቅምንና የህዝብን ክብር ባከበረ መልኩ የሕዝብ ድምፅ ለማግኘት የምረጡኝ ቅስቀሳ እያካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ክርክር ማካሄድ የስልጡን ፓርቲዎች ተግባር መሆኑንም ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም