የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት መሰረት ባደረገ መልኩ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት መሰረት ባደረገ መልኩ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት አለበት
ዲላ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት የሚመጥንና ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብቷን መሰረት ባደረገ መልኩ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄዋ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት እንዳለባት ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለውን ምጣኔ ሃብቷን የሚሸከም የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄዋ ባጠረ ጊዜ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ታምራት በየነ(ዶ/ር) እንዳሉት የባህር በር የኢትዮጵያን ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት የሚያጠናከር በመሆኑ ባጠረ ጊዜ ምላሽ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነው።
በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለው የህዝብ ቁጥር ብቻ ሳይሆን የወጭ ንግዱም መሆኑን አንስተው ለዚህም በግብርና ዘርፍ በተለይ በቡና እንዲሁም በማዕድን ልማት የተገኘው ገቢ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት አዋጭና አመች ለሆኑ ሁኔታዎች ቅድሚያ ይሰጣል ያሉት ምሁሩ በዚህም የራሳቸው የባህር በር ያላቸው ሀገራት ተወዳዳሪነታቸውና ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የቀይ ባህር ቀጣና ዓለምን በንግድ፣ በሰላምና በዲፕሎማሲ በማስተሳሰር ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ ተመራጭ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት የሚመጥንና ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብቷን መሰረት ባደረገ መልኩ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የባህር በር ከምጣኔ ሀብት እድገት ባሻገር ራስን መጠበቅና ዓለም አቀፍ ትስስርን ማጠናከሪያ መንገድ በመሆኑ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነ-ትምህርት ዘርፍ ምሁሩ ፍሬዘር ዓለሙ(ዶ/ር) ናቸው።
የባህር በር አጀንዳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘቱን አንስተው ይህም የኢትዮጵያ ጥያቄ ፍትሃዊና የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር በመግፋት በቀጣናው የሚያተርፍ ሀገር የለም ያሉት ምሁሩ ለአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ እድገትና ለቀጣናው ሰላም ሲባል ኢትዮጵያ በአፋጣኝ የባህር በር ማግኘት እንዳለባት አስረድተዋል።