በአሪ ዞን በዘንድሮ የበልግ አዝመራ ከ51ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በአሪ ዞን በዘንድሮ የበልግ አዝመራ ከ51ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል
ጂንካ፤ የካቲት 20/2018 (ኢዜአ)፡-በአሪ ዞን በዘንድሮ የበልግ አዝመራ ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለግብርና ሥራ ተስማሚ ስነ-ምህዳር፣ በቂ ውሃ እና ለም መሬት ካለባቸው አካባቢዎች አንዱ የአሪ ዞን ነው።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሪ ዞን ያለውን ሀብትና ፀጋ አሟጦ በማልማት የአርሶ አደሮችን ኑሮ ለመለወጥ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
በዞኑ በዘንድሮ የበልግ አዝመራ ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስብጥር አመራረት ዘዴ ጥራጥሬዎችን እና ሆርቲካልቸር በማጣመር ለማልማት መታቀዱን ገልፀው፣ እስካሁንም ከ 41 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በበልግ አዝመራው ከ117ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ በልማቱም የሆርቲካልቸር ምርቶችን ሳያካትት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘትመታቀዱንም አመልክተዋል፡፡
የበልግ አዝመራ ውጤታማነትን ለማሳደግም በሕብረት ሥራ ዩኒየኖች አማካኝነት የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑንም አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ ውስንና የተለመዱ ሰብሎችን ብቻ ያለማ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፣ አሁን ላይ የስብጥር አመራረት ዘዴን በመከተል በአነስተኛ መሬት የተሻለ ጥቅም የሚያገኝበት አሰራር በመተግበር ውጤታማ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
በዞኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ልምድ እያደገ ከመምጣቱ ባለፈ አርሶ አደሩ ሰብሎችን በኩታ ገጠም ማልማት በመጀመሩ የሰብል ምርታማነት በእጅጉ እያደገ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ቀደም ሲል ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ምርጥ ዘሮችን በአርሶ አደሮች ማሳ ማልማት መጀመሩን ገልፀው፣ በአሁኑ ወቅት የተሻሻሉ የስንዴ፣ የበቆሎና የማሽላ ዘር ብዜት በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ ደቡብ አሪ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑት አቶ ማሙሽ አዲሱ በዘንድሮ የበልግ አዝመራ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ እንዳሉ ገልጸዋል።
በበልግ አዝመራ መሬታቸውን ለሦስት ጊዜ አርሰውና አለስልሰው ለዘር ሥራ ማዘጋጀታቸውን ገልፀው፣ በዘንድሮ የበልግ አዝመራ በቆሎ፣ ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ካሮትና መሰል ሰብሎችን በስብጥር ለማልማት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
በግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ምክረ ሀሳብ መሰረት ጥራጥሬን ከአትክልትና ፍራፍሬ ጋር በማጣመር በስብጥር እያለሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በዞኑ የባካ ዳውላ አሪ ወረዳ አርሶ አደር ግዛው አለሙ ናቸው።
ጥራጥሬዎችን ከአትክልትና ፍራፍሬዎች ጋር አጣምሮ ማልማት ምርታማነትን በመጨመር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድግ በተግባር አይተናል ብለዋል።