መቱ ዩኒቨርሲቲ በሚያካሄደው ማህበረሰብ ተኮር የጥናትና ምርምር ስራዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መቱ ዩኒቨርሲቲ በሚያካሄደው ማህበረሰብ ተኮር የጥናትና ምርምር ስራዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እያደረገ ነው
መቱ፤ የካቲት 20/2018 (ኢዜአ):- መቱ ዩኒቨርሲቲ በሚያካሄደው ማህበረሰብ ተኮር የጥናትና ምርምር ስራዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት የግብርና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪና መምህር ነዚፍ ሀምዛ ለኢዜአ እንዳሉት ዩኒቨርሰቲው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በማካሄድ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት እየሰራ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በግብርና መስኮች ጥናትና ምርምር እያካሄደ ሲሆን ውጤቶችንም ወደ ተጨባጭ ስራ ለመቀየር ዘጠኝ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ለተግባራዊነቱ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የሰብል እና የሆርቲካልቸር ምርጥ ዘር ዝግጅትና ብዜት፣ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ እንዲሁም ቨርሚ ኮምፖስት ቴክኖሎጂን ማስረጽ እንደሚገኙበት አስረድተዋል።
በተለይ በሰብል ልማት እና በሆርቲካልቸር ከአከባቢው የአየር ንብረት ጋር ተስማሚ እና ምርታማነታቸው የተረጋገጠ ዝርያዎችን ለማባዛትና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የፕሮጀክቶቹ ዋና ዓላማ የመማር ማስተማር ስራውን በተግባር የተደገፈ ከማድረግ ባለፈ የአካባቢው ማህበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በውስጥ አቅም ራሳቸውን እንዲችሉ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ለማሳካት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ዩኒቨርሲቲው የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እና የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናን እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል አስረድተዋል።
በዩኒቨሲቲው የዕጽዋት ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ መምህር ምስጋኑ ዋቅጅራ በበኩላቸው በምርምር የተገኘ ምርጥ የበቆሎ ዝርያን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም በ2017/2018 መኸር ከኢትዮጵያ የግብርና ግብአቶች ኮርፖሬሽን የነቀምቴ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር በ30 ሔሄታር መሬት ላይ የማባዛት ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት የምርት መሰብሰብ ስራው ተጠናቆ ለዘር የሚሆን 600 ኩንታል በቆሎ በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሆርቲካልቸር ዘርፍ መምህርና ተመራማሪ ሳሙኤል ታዬ ዩኒቨርሲቲው በግብርናው ዘርፍ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የችግኝ ጣቢያዎችን በማዘጋጀት ለመማር ማስተማር፣ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለማህበረሰብ አገልግሎትና ትስስር ስራዎቹ እየተጠቀመበት መሆኑን አንስተዋል።
ይህም ዩኒቨርሲቲው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ሀገራዊ ግቦች ለማሳካት የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣት ተመስገን ሂካ፣ መልካሜ ተሾመ እና አቶ ብርሃኑ ማሞ በፕሮጀክቱ ችግኝ ጣቢያዎች የስራ እድል የተፈጠረላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ሲሆኑ በስራው በሚያገኙት ገቢ ሕይወታቸውን እየመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ያገኙትን ልምድ በመታገዝ የራሳቸውን ችግኝ ጣቢያ በማቋቋም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።