በክልሉ በተያዘው የበጋ ወራት ከ64 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና የውሃ ጥበቃ የተፋሰስ ልማት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተያዘው የበጋ ወራት ከ64 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና የውሃ ጥበቃ የተፋሰስ ልማት እየተከናወነ ነው
ጋምቤላ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በተያዘው የበጋ ወራት ከ64 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና የውሃ ጥበቃ የተፋሰስ ልማት በመከናወን ላይ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮ ኃላፊው አድሮው ቱት ለኢዜአ እንደገለጹት ምርታማነትን ለማሳድግ በበጋው ወራት የተጠናከረ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በክልሉ በሚገኙ ሶስቱም ዞኖች የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተፋስ ልማት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የተፋሰስ ልማት ስራዎች በክልሉ በሚገኙ 13 ወረዳዎች በተመረጡ 101 ተፋሰሶች በመደበኛና በፕሮጀክቶች ከ64ሺህ ሄክታር በላይ በሚሸፍን መሬት ላይ እየተከወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በተፋሰስ ልማት ስራው ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በተጓዳኝ ባለፈው ክረምትና ከዚያ በፊት በአረንጓዴ አሻራ ልማት ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ እየተደረገ እንደሆነም አክለዋል።
በክልሉ በበጋው ወራት እየተካሄደ ያለውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በመጪው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስነ-ህይወት ለማላበስ በ66 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የማፍላት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመጪው ክረምት በሚከናወነው ለአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ከሚዘጋጁት ችግኞች መካከል ከ8 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ከደንነት በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።