የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተመጣጠነ ምግብን በቤተሰብ ደረጃ ተደራሽ በማድረግ በኩል ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተመጣጠነ ምግብን በቤተሰብ ደረጃ ተደራሽ በማድረግ በኩል ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተመጣጠነ ምግብን በቤተሰብ ደረጃ ተደራሽ በማድረግ በኩል ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሎች የዘርፉ አመራሮች ገለጹ።
መርሃ ግብሩ በዋናነት የእንስሳት ተዋጽኦ ወተት፣ እንቁላል፣ ሥጋ፣ ማር እና የዓሳ ሃብት ምርታማነትን በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመ ሀገር አቀፍ የልማት ግብ ነው።
የምግብ ዋስትና እና ሥርዓተ ምግብን እና የእንስሳት ምርታማነትን ማሻሻል፣ በቤተሰብ ደረጃ በምግብ ራስን መቻል፣ በከተማና በገጠር የምርትና ገበያ ትስስርን በማሳለጥ የስራ ዕድል መፍጠር እንዲሁም ገቢ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የመርሃ ግብሩ ወሳኝ ዓላማዎች ናቸው።
በዚህም በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሻሻል የሸማቹን ማህበረሰብ የምርት ፍላጎት ምላሽ በመስጠት ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።
የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አሰፋ ፎና ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በክልሉ ያለውን የእንስሳት ሀብት ምርታማነት ለማሻሻል በሁሉም አካባቢዎች በውጤታማነት እየተተገበረ ይገኛል።
ሀገራዊ ኢኒሼቲቭን መነሻ በማድረግ በተለይም በወተት፣ በእንቁላልና ዶሮ፣ በማር ምርት እንዲሁም በዓሳ ሀብት ልማት ላይ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውንና በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በዘርፉ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል እና የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ ታመነ በቀለ በበኩላቸው፣ የሌማት ትሩፋት ውጤታማነት የአካባቢው ማህበረሰብን ተጠቃሚ አድርጓል።
መርሃ ግብሩ ምርትን በማትረፍረፍ ሸማቹ ማህበረሰብ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝና ገበያው እንዲረጋጋ ማድረጉን ጠቁመዋል።
መርሃ ግብሩ የከተማ ነዋሪዎችን ከሸማችነት ወደ አምራችነት የቀየረ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በተለይም በዶሮ እርባታ ዘርፍ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎች ቁጥር መጨመሩንና የጫጩቶች ስርጭትም ወደ ሚሊዮኖች ማደጉን ጠቅሰዋል።
ይህም ከምግብ ዋስትና ባለፈ፣ የተመጣጠነ ምግብን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ስርዓተ ምግብን ለማስተካከል አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻርም ለበርካታ ዜጎች በግብርናው ሰንሰለት ውስጥ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አርሶ እና አርብቶ አደሩን እንዲሁም ሸማቹን የሚያገናኝ ጠንካራ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።