የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማስከበር የማይናወጥ የጋራ አጀንዳ ነው - የምጣኔ ሃብት ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማስከበር የማይናወጥ የጋራ አጀንዳ ነው - የምጣኔ ሃብት ምሁራን
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማስከበር የማይናወጥ የጋራ አጀንዳ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መልክዓምድራዊ አመክንዮ ያቀረበችው አስተማማኝ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ያለመ መሠረታዊ አጀንዳ ነው።
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄው ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችል በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ነው።
ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን በማስመዝገብ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የንግድ ሥርዓትን በማሳለጥ ዓለምዓቀፍ ተወዳዳሪነት ፍላጎትን ጭምር ያነገበ ነው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደገለጹት፤ አስተማማኝ የባሕር በር ባለቤትነት ለአንድ ሀገር የንግድና ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
ኢትዮጵያ ከባሕር በር እንድትርቅ የተፈጸመባት የታሪክ በደልም በአጠቃላይ ፈጣን የንግድና ኢኮኖሚ ዕድገቷ ላይ ዘርፈ ብዙ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ደረጀ ደጀኔ፤ የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ዓለምአቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነት አቅምን እያጎለበተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም አስተማማኝ የባሕር በር አለመኖሩ የሚመነጨውን ከፍተኛ ኢኮኖሚ መልሶ እየበላው እንደሚገኝ አንስተዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ግዙፍ የንግድ እንቅስቃሴ የሚመጥን አስተማማኝ የባሕር በርና አማራጭ የወደብ አገልግሎት ማግኘት ቅንጦት ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል።
ሌላው የምጣኔ ሃብት ምሁር ጀማል መሐመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አስደማሚ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኝ ሀገር ናት ብለዋል።
አስተማማኝ የባሕር በር አለመኖሩ ግን ሀገር የምታመነጨውን ግዙፍ የንግድ እንቀቅስቃሴ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማቀጨጭ በዜጎች ተጠቃሚነት ላይ ቀጥተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደምጣኔ ሃብት ምሁራኑ ገለፃ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገርን ፈጣን ዕድገትና ግዙፍ የንግድ እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረገ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትም ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን በማጠናከር የጋራ ዕድገትን ማሳለጥ የሚያስችል የጋራ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።
130 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር በር ሊኖራት ይገባል ያሉት ምሁራኑ፤ ዜጎችም የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማስከበር የማይናወጥና የህልውና ጉዳይ የሆነ የጋራ አጀንዳ መሆኑን አስረድተዋል።