ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የዓሣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የዝርያ ማሻሻልና ተጓዳኝ ስራዎች እያከናወነ ነው

አዳማ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የዓሣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የዝርያ ማሻሻልና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ተሾመ ቦጋለ ለኢዜአ እንደገለጹት የዓሣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በዓሣ ዝርያ ማሻሻያ ላይ ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በተለይ እየተተገበረ ያለውን የዓሣ ልማት ኢንሼቲቭ ለማሳካት ምርቱን የሚጨምሩ ዝርያዎችን በስፋት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ የውሃ አካላት በሙሉ የዓሣ ምርት መያዝ አለባቸው የሚል ግብ ተቀምጦ በዝርያ ማሻሻያ ላይ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በምርምር ማዕከላቱ የዓሣ ጫጩት የማባዛት ስራ እየሰራ መሆኑንና የተባዙ የዓሣ ጫጩቶችን ለአርሶ አደሩ በነፃ እየተሰራጨ መሆኑንም አክለዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከ1 ሚሊየን በላይ የዓሣ ጫጩቶች መሰራጨታቸውን ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 5 ሚሊየን የዓሣ ጫጩቶች ለማሰራጨት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የባቱ የዓሣ ምርምር ማዕከልን ጨምሮ በኢንስቲትዩቱ ስር በሚገኙ የምርምር ማዕከላት ብዛት ያላቸው የዓሣ ጫጩት ዝርያዎች መባዛታቸውን ጠቁመው የዓሣ ጫጩት ብዜት ስራው በቤተ ሙከራና በኩሬ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዝርያ ማሻሻያ ስራዎች በተጓዳኝ ከዓሣ እርባታ ጋር በተያያዘ የእውቀትና የአሰራር ክህሎት ስልጠናና አቅም ግንባታም እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በሀገር ደረጃ የተያዘውን በምግብ ራስን የመቻልና  የስነ ምግብ ስርዓትን ለማስረፅ የዓሣ ሀብት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

በዚህም የህፃናት የአእምሮ  እድገት እንዲጎለብት፣ የመቀንጨርና መቀጨጭ ችግሮችን ለመቅረፍ ዓሣ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም