ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018 (ኢዜአ)፦‎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ጋር ተወያይተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በአዘርባጃን ባደረጉት የመጀመሪያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ላደረጉላቸው ሞቅ ያለ እና የተከበረ አቀባበል ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 




‎ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአቪዬሽን ዘርፍ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በነፃ የንግድ ቀጣናዎች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በአዘርባጃን አቻው መካከል በተደረጉ የኢኮኖሚ ትብብሮች ላይ በመመስረት የሀገራቱ አጋርነት በየጊዜው እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል። 


 

የትብብር ዘርፎቹ ለሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር መሠረት የጣሉ ሲሆን፣ ዛሬ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በተደረገው  ጥልቅ ውይይትም ግንኙነቱን እና ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል። 


 

የሀገራቱ መሪዎች በዛሬው ዕለትም በመከላከያ እና በሌሎች ዘርፎች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነዶች ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም