በምዕራብ ወለጋ ዞን የሰፈነው ሰላም የሕዝብ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ዞን የሰፈነው ሰላም የሕዝብ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሯል
ጊምቢ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ወለጋ ዞን የሰፈነው ሰላም የሕዝብ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ዕድል መፍጠሩን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
የዞኑ አመራሮች በዞኑ ውስጥ ግንባታቸው እየተከናወነ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ተመልክተዋል።
በአመራሮቹ ከተጎበኙት ፕሮጀክቶች መካከል በቤጊ ወረዳ ኮቦር ከተማ የሚገኘው የግብርና ልማት ማዕከል፣ የእንስሳት እርባታና የንብ ማነብ ማዕከላት እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተሊላ ተረፋ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የዞኑ ነዋሪዎች የሚያነሱትን የልማት ጥያቄዎች የመመለስ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸውም ገልጸው በዞኑ የሰፈነው ሰላም ለልማት ስራዎች መፋጠን እገዛ አድርጓል ብለዋል።
በተለይም በግብርና ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ ኢኒሼቲቮች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሸል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቀጣይም በዞኑ የተመዘገቡ የልማት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ህዝቡን ያሳተፈ የሰላምና የልማት ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በዞኑ በግንባታ ላይ ከሚገኙ መሰረተ ልማቶች መካከል መንገድ፣ ድልድይ፣ የመስኖ አውታር፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት እንደሚገኙበትና በተያዘው የበጀት ዓመት ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።