በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሲዳማ ቡና በሊጉ 14 ጨዋታዎችን አድርጎ በአምስቱ ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በ14 ጨዋታዎች ላይ 14 ግቦችን ሲያስቆጥር 18 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ18 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ እስከአሁን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች በ11ዱ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ 37 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አምስት ጎሎችን አስተናግዷል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ35 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ቡድኖች ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዘገብ ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር መቻል ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
መቻል 14 ጨዋታዎችን አከናውኖ በዘጠኙ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
23 ጎሎችን ሲያስቆጥር ሰባት ግቦች ተቆጥረውበታል። መቻል በ30 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች መካከል ስምንቱን ያሸነፈው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 23 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ግቦችን አስተናግዷል።
ሃዋሳ ከተማ በ28 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ቡድኖች ከ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የአቻ ውጤት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
ሸገር ከተማ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።
ሸገር ከተማ በ27 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። አዳማ ከተማ በ16 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።