ሶስት አስርት ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ወዳጅነት - ኢዜአ አማርኛ
ሶስት አስርት ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ወዳጅነት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአዘርባጃን ሪፐብሊክ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ማድረግ ጀምረዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአዘርባጃን ሪፐብሊክ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር ማሳያ ነው። ይህ ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የላቀ እና ትርጉም ያለው ደረጃ ያደርሰዋል።
ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት አዘርባጃን እ.አ.አ በ1991 ነጻነቷን ማግኘቷን ተከትሎ ነው። የሀገራቱ ግንኙነት ከእ.አ.አ 1990ዎች መግቢያ አንስቶ እያደገ መጥቷል። አዘርባጃን እ.አ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ኤምባሲ የከፈተች ሲሆን ይህም የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ትብብር እንዲጠናከር በር ከፍቷል።
በቱርክዬ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስራ የሚሸፍን ሲሆን ፖለቲካ፣ ትምህርት እና ባህል ሀገራቱ ካላቸው የትብብር መስኮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየጎለበተ መምጣቱን ከሚያመላክቱ ጉዳዮች መካከል በባለብዙ ወገን መድረክ በገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ (ናም) መድረክ በትብብር እየሰሩ መገኘታቸው ተጠቃሽ ነው።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2019 በአዘርባጃን ባኩ በተካሄደው 18ኛው የገለልተኛ ሃገራት ንቅናቄ (ናም) ጉባኤ ላይ ተሳትፋለች። የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ 120 አባል ሃገራትን ያቀፈና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዓለም ሀገራትን በአባልነት የያዘ ስብስብ ነው።
የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ወዳጅነት የደቡብ ደቡብ ትብብር ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል። በሀገራቱ መካከል ተከታታይ የሆኑ የባህል ልውውጥ መድረኮች ተካሄደዋል። ለዚህም እ.አ.አ በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአዘርባጃን የትምህርት እድል አግኝተው ይከታተሉ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
ከኢኮኖሚ አንጻር እ.አ.አ በ2017 በአዘርባጃን የተካሄደው የሁለቱ ሀገራት የቢዝነስ ፎረም ተጠቃሽ ነው። በወቅቱ ጨርቃጨርቅን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
በወቅቱ ሀገራቱ እርስ በእርስ ያላቸውን የንግድ ልውውጥ ምጣኔ ለማሳደግ የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ባለስልጣናት መካከል የሚደረጉ የጉብኝት ልውውጦች እያደጉ መጥተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በአዘርባጃን ጉብኝት ማድረጋቸወ ይታወሳል። ኢትዮጵያና አዘርባጃን በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ማሳደግና በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውም እንዲሁ።
ምክክሩ እጅግ ውጤታማ የነበረ ሲሆን የሁለቱን ሀገራት ህዝብ ዕድገት እና ብልፅግና በመደጋገፍና በትብብር መንፈስ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውም በወቅቱ ተገልጿል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከአዘርባጃን የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ኮሎኔል-ጀነራል ኢይቫዞቭ ቪላያት ሱለይማን ጋር በነበራቸው ውይይት የደህንነት ጉዳዮችን ጨምሮ የኢትዮጵያን እና አዘርባጃን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብሮችን ማጠናከር የሚያስችሉ ቀጣይ ስራዎች ላይ መክረዋል።
በውይይቱም በመረጃ፣ በፀጥታና ደህንነት ዘርፎች የጋራ ትብብር አቅም ግንባታና ሌሎች ጉዳዮች ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመፈጸም መስማማታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መግለጻቸው ይታወሳል።
እ.አ.አ በ2017 በወቅቱ የአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ኤልማር ማማድያሮቭ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውና የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በቋሚነት የፖለቲካ ምክክር ማድረግ የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።
የአዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስ እና ማኅበራዊ ፈጠራ ተቋም ሊቀ መንበር ኦልቪ ሜዲዬቭ የብሔራዊ ቤተመንግሥት እና የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ጎብኝተዋል። ኦልቪ ሜዲዬቭ በወቅቱ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጋር ተወያይተዋል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በጥር ወር 2017 ዓ.ም በአዘርባጃን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያልቺን ራፊየቭ የተመራ ልዑክ ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸውም ኢትዮጵያ ወደ አዘርባጃን የምትልካቸው ምርቶች ብዝኀነትን ለማሳደግና ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኗን ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ አዘርባጃን ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ሰሊጥ፣ የተቆላ ቡና፣ ተልባ፣ የፍየል እና የበግ ሥጋን ጨምሮ ሌሎች ምርቶች እንደሚገኙበት ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአዘርባጃን የመከላከያ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ቩጋር ሙስታፋይ የተመራ ልዑክ በህዳር ወር 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ከመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር መስማማታቸው ይታወሳል።
በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ንግድ ትብብር ላይ ያተኮረው ሶስተኛ የኢትዮ-አዘርባጃን የውይይት መድረክ በጥር ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ከውይይቱ በኋላ ሀገራቱ የኢኮኖሚ እና የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳደግና ተጨማሪ እድሎችን መፈተሽ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም መግባባት ላይ ደርሰዋል።
29ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 29) በህዳር ወር 2017 ዓ.ም በአዘርባጃን መካሄዱ ይታወቃል። በጉባኤው ኢትዮጵያ በፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተመራ ልዑክ ተሳትፎ አድርጋለች።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ልዑክ ከአዘርባጃን ባለስልጣናት ጋር በመወያየት ሀገራቱ በአካባቢ ጥበቃ፣ አየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና አረንጓዴ ልማት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በቁርጠኝነት ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በሀገራቱ መካከል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተደረጉ ውይይቶችና የልምድ ልውውጦች የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር እየጠነከረ መምጣቱን ያሳያል። ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ግብርና፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ትምህርት እና ባህልን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ትብብራቸውን ለማጠናከር ይሻሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአዘርባጃን ሪፐብሊክ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ማድረግ መጀመራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የኢትዮጵያ እና የአዘርባጃን ግንኙነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጠነከረ መምጣቱን የገለጸው ጽህፈት ቤቱ ለዚህም ጉልህ ማሳያው በጠንካራ ትብብር የቀጠለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጎልቶ እንደሚታይ አንስቷል።
የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአዘርባጃን ሪፐብሊክ ጉብኝትም የዚሁ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር ማሳያ መሆኑን ጠቁሟል። ይህ ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የላቀ እና ትርጉም ያለው ደረጃ እንደሚያደርስ ይጠበቃል ሲልም ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጉብኝት በመሪ ደረጃ የሚደረግ መሆኑ በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ውስጥ ትልቅ ትርጉም ይሰጠዋል።
ሶስት አስርት ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚሸጋገር የቅርብ ዓመታት ውይይቶች እና ጉብኝቶች ማሳያ ናቸው።