ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁትን የፖርቹጋል አምባሳደርን አሰናበቱ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁትን የፖርቹጋል አምባሳደርን አሰናበቱ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የፖርቹጋል አምባሳደር ሉዊሳ ፋራጎሶ አሰናብተዋል።
በዚሁ ወቅት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ አምባሳደሯ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በተለያዩ ዘርፎች የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በተለይም አምባሳደሯ በቱሪዝም፣ በባህልና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ የነበራቸው ከፍተኛ ሚና በቀጣይ የትብብር መስኮችም ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ተሰናባቿ የፖርቹጋል አምባሳደር ሉዊሳ ፋራጎሶ በበኩላቸው፤ የኢትዮ-ፖርቹጋል ግንኙነት ከ500 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ወዳጅነትን ያሳለፈ ነው ብለዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ የስራ ቆይታቸውም በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በቱሪዝምና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዘርፎች ትስስሩን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን እንዳከናወኑ ገልጸዋል።
የሀገራቱ ተቋማዊ ግንኙነት መጠናከር አስፈላጊ ነው ያሉት አምባሳደሯ፤ በአዲስ አበባና በፖርቶ ከተሞች መካከል የሚካሄደው የቀጥታ የአየር በረራ አገልግሎትም ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር በረራ አገልግሎቱም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የሀገራቱን የትምህርትና የባህል ትብብር መስክ ይበልጥ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም የሁለትዮሽ ትብብሩን ይበልጥ ለማሳደግ በሀገራቱ የሚገኙ ሃብቶችንና የልማት ዕድሎችን የሚያስተዋውቁ የምክክር መድረኮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይም በአውሮፓ ሕብረት የግሎባል ጌትዌይ ማዕቀፍ ሥር የንግድ ፎረም ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት ለቀጣይ ትብብሮች ተስፋ ሰጪ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።