ቀጥታ፡

የመሬት እንቅስቃሴ አደጋዎችን ለመቀነስ የመከታተያ ማዕከላት ማስፋፋት ያስፈልጋል - የዘርፉ ምሁራን

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ የመሬትመንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ አደጋዎችን ለመቀነስ የመከታተያ ማዕከላት ማስፋትና የህዝብን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ "የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ አደጋ በኢትዮጵያ ስጋትና መፍትሔዎች" በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።


 

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በተሰናዳው መድረክ የታደሙት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሀንስ፤ ምሁራን በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸውን ሚና ማላቅ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም በተለያዩ ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለሕትመትና ተደራሽነት እንዲበቁ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በኢትዮጵያ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸውን መፍትሔ አመላካች የጥናትና ምርምር ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጂኦ-ፊዚክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይንስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ፤ የመሬት እንቅስቃሴ በተፈጥሮ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለዋል።


 

በመሬትና በብዝኅ ህይወት ላይ የሚፈጥረው የገጽታ ለውጥም በህዝብ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ አኗኗር ሥርዓት ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የመሬት እንቅስቃሴዎችንም በመከታተል በተለያዩ ጊዜያት ህዝቡን የማስገንዘብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ አደጋዎችን አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም የማዕከላትን መረጃ ማጠናቀር አቅም ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።


 

‎የምህንድስና የመወያያ ሃሳብ ያቀረቡት የጂኦቴክኒክ ኢንጅነሪንግ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አስራት ወርቁ በበኩላቸው፤ የመሬት እንቅስቃሴ አደጋዎችን ለመቀነስ የግንባታ ጥራትን ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።

የህንፃና ተያያዥ መሰረተ ልማት ገንቢ ተቋማትና መሃንዲሶችም ከመሬት ሳይንስ ተመራማሪዎች ጋር በመቀናጀት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


 

የመሬት መንቀጥቀጥ ማህበራዊ ገጽታን አስመልክቶ ጽሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ተገኝ ገብረእግዚአብሔር፤ የስምጥ ሸለቆ የከተሜነት መስፋፋት ለመሬት እንቅስቃሴ አደጋ ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋል ብለዋል።

ለዚህም የሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር የቅድመ ማስጠንቀቂያና የመሠረተ ልማት ጥራትን ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም