ቀጥታ፡

ትውልዱ ራሱን በሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የጥበብ ስራዎች ውስጥ በማየት የሀገሩን አርት ለማሳደግ መትጋት አለበት

አምቦ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ ትውልዱ ራሱን በሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የጥበብ ስራዎች ውስጥ በማየት የሀገሩን አርት ለማሳደግ ጠንክሮ መስራት አለበት ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) አስገነዘቡ።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የትውልድ ስፍራ ያስገነባው ትምህርት ቤትም ለምረቃ መብቃቱ ተመልክቷል።


 

የሎሬቱን 20ኛ ዓመት ህልፈተ ህይወት መርሃ ግብርን መነሻውን በአዲስ አበባ ራስ መኮንን ድልድይ (70 ደረጃ) ከሚገኘው የሎሬቱ መታሰቢያ ሐውልት ጋር በማድረግ ወደ ሎሬቱ ትውልድ ከተማ አምቦ በማቅናት በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ-ጥበብና ስነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት መርሃ ግብሩ የተዘጋጀው በዋነኝነት ሀገር ለጥበብ ሰዎች ያላትን ክብር ለመግለፅ ነው ብለዋል።

እንዲሁም የሎሬቱን የጥበብ ትሩፋትና በጎ አሻራ ለወጣቱ ትውልድ ለማስተላለፍ መሆኑንም አመልክተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም “የአሁኑ ትውልድ ራሱን በሎሬቱ የጥበብ ስራዎች ውስጥ በማየት የሀገሩን አርት ለማሳደግ ጠንክሮ መስራት አለበት” ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ከዚህ በኋላ በየዓመቱ የሎሬት ፀጋዬን የአርት ስራዎች የሚዘክርና የሚያሳዩ ስራዎችን በቋሚነት ለመስራት ማቀዱንም ይፋ አድርገዋል።


 

በዛሬው ዕለትም በሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን 20ኛ የዕረፍት መታሰቢያ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባው የኢፈ-ቦሩ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ትምህርት ቤቱን ከማስገንባት ባለፈ፣ ለተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደት ግብዓት የሚሆኑ ልዩ ልዩ ድጋፎችን አድርጓል።

በዚህም መሠረት ለትምህርት ቤቱ አገልግሎት የሚውሉ ላፕቶፖች፣ ፕሪንተሮችና ሌሎች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ጨምሮ በጠቅላላው 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ በስጦታ መልክ አበርክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደራራ ከተማ በበኩላቸው ሎሬቱ የሀገራችንን አርት ለዓለም ያስተዋወቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ቢሮው መሰል የጥበብ ሰዎችን ለማፍራት የሚያስቸሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው ይህንንም ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት አርቲስቶችም የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንን አርአያነት በመውሰድ፣ የሀገራችንን ጥበብ አሁን ካለበት ለማሳደግ ተባብረው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

አርቲስት አበበ ባልቻ እንደገለፀው፤ የሎሬቱ የጥበብ ሥራዎች በርካታ አርቲስቶችን በማፍራት በሀገራችን የጥበብ እድገት ውስጥ የማይረሳ አሻራ አኑረዋል።

አርቲስቱ አክሎም በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ስም የተሰየመውን የኢፋ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሌሎች አርቲስቶችን በማስተባበር በየዓመቱ በመምጣት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብሏል።

ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የኢትዮጵያን ጥበብ ከማሳደግ ባለፈ የአፍሪካ የጥበብ እድገት በዓለም መድረክ እንዲታይ ያደረገ መሆኑን የገለፀው ደግሞ አርቲስት ተፈሪ አለሙ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያን እንድንወድ ያደረገ ታላቅ አርቲስት ነው ሲልም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም