ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ተወሰነ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ የሰላም አማራጭ ተቀብለው የተመለሱ እና በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ስር ሲያገለግሉ የነበሩ የቀድሞው የመንግሥት ሰራተኞች ወደ መንግሥት ስራቸው እንዲመለሱ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፏል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት ባካሔደው 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባው የሰላም አማራጭን ተቀብለው በተመለሱና ቀደም ሲል በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ሲያገለግሉ በነበሩ ሠራተኞች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።


 

የክልሉ መንግሥት ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማረጋገጥ ባለው ጽኑ ቁርጠኝነት፣ ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ አካላት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት በመንግሥት ጥሪ፣ በድርድርና በውይይት የሰላም አማራጭን መርጠው የተመለሱና የተሃድሶ ሥልጠና የወሰዱ የቀድሞ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ምክር ቤቱ ወስኗል።

ይህ ውሳኔ የክልሉ መንግሥት ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያለውን ዝግጁነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።

በቀጣይም ለክልሉ ዕድገትና አንድነት መሰል የሰላም ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም