በክልሉ መንግሥት ተገንብተዉ ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚነታችንን የሚያሳድጉ ናቸው- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ መንግሥት ተገንብተዉ ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚነታችንን የሚያሳድጉ ናቸው- ነዋሪዎች
ሆሳዕና፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ) ፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ ፕሮጀክቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን የሀዲያ ዞን ነዋሪዎች ገለፁ፡፡
በዞኑ በተለያዩ መዋቅሮች የተገነቡ የመንገድ፣ የመስኖና የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል፡፡
የዞኑ ነዋሪዎች በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ መንግሥት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ ፕሮጀክቶች የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው፡፡
አርሶ አደር ከድር ዋበላ በሀድያ ዞን ሻሸጎ ወረዳ ዶኢሻ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በአካባቢው ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የመስኖ ፕሮጀክት ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።
በተለይም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የነበረውን የእርሻ ስራ እስከ ሶስት ጊዜ በማሳደግ የተሻለ ምርት ለማግኝት እንደሚረዳቸውም ነው የገለጹት።
በሌሞ ወረዳ አምቢቾ ጎዴ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሸጋ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ መመረቁ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት ይጓዙ የነበረውን ረጅም ርቀት እንዳስቀረላቸው ነው የሚናገሩት።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለፁት የክልሉ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረጉን ይቀጥላል ።
በክልሉ ፈጣን እድገትን ለማረጋገጥ ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
በክልሉ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ልማት አጠናክሮ በማስቀጠል የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያብራሩት።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑርዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሃዲያ ዞን ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የመንገድ፣ የአነስተኛ መስኖና የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ የማህበረሰቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ የመለሱና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡