ቀጥታ፡

ለብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ሥፍራዎች ልማት የተሰጠው ትኩረት ከቱሪዝም ዘርፉ የበለጠ ለመጠቀም ያስችላል

ባህር ዳር ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡-ለብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ሥፍራዎች ልማት የተሰጠው ትኩረት ከቱሪዝም ዘርፉ የበለጠ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በሀገሪቱ 29 ብሔራዊ ፓርኮችና 87 ዓይነት ጥብቅ ስፍራዎች ይገኛሉ ብለዋል።

የጥብቅ ስፍራዎችን ማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የአካባቢ ጥበቃ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ጨበራ ጩርጩራ፣ አዋሽ እና ባሌ ብሔራዊ ፓርኮች ያሉ ሥፍራዎች ላይ የተሰሩ የልማት ሥራዎች ለቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም እንዲሁ።

በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የሚታየውን ልዩ የዱር እንስሳት እንቅስቃሴ ለቱሪዝም መስህብነት ለማዋል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ነው ያብራሩት።

በፓርኮች ውስጥ የሚስተዋሉትን ልቅ የእንስሳት ግጦሽ፣ የደን ጭፍጨፋ፣ ሕገ-ወጥ አደንና የእርሻ መስፋፋት ችግሮችን ለማስወገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ብለዋል።

መንግስት የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት ረገድ የሰጠው ልዩ ትኩረት ዘርፉ በፍጥነት እያደገ እንዲመጣ ማስቻሉንም ገለጸዋል።


 

የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ በበኩላቸው፤ በክልሉ የእንሰሳትና የብዝሃ ሕይወት የመጠበቅ ስራ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚስተዋሉ ሰደድ እሳት፣ ህገወጥ እርሻ፣ ደን ጭፍጨፋ፣ ሕገ-ወጥ አደንና መሰል ተግባራትን ሕብረተሰቡን በማስተባበር የመጠበቅ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ፓርኩ ለአካባቢው ማሕብረሰብ ያለውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት ቀደም ሲል 136 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የነበረውን የፓርኩ ይዞታ ወደ 412 ስኩዌር ኪሎ ሜትር እንዲሰፋ መደረጉን አስታውሰዋል።

ፓርኩን የማስፋት ስራ በዩኔስኮ መመዝገብ ስላለበት ይህንኑ ተግባር እውን ለማድረግ በጥናት ላይ መሰረት ያደረገ ሰነድ ተዘጋጅቶ መቅረቡን ተናግረዋል።


 

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት  አስማማው ዘገየ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ በምርምርና በማሕበረሰብ አገልግሎት ፓርኩን እያገዘ ነው።

የቱሪዝምና ቅርስ አስተዳደር የትምህርት ክፍል በመክፈት ተማሪዎች በተግባር የታገዘ ትምህርት እንዲወስዱ ከማድረግ ባሻገር ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሃብቱን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቀደም ሲል የተካሄደው የይዞታ ማስፋት ስራ የአካባቢውን ማሕበረሰብ የበለጠ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ የፓርኩ የሕግ ማስከበር ቡድን መሪ ሲሳይ ሰለሞን ናቸው።


 

በማስፋት ስራውም ቀደም ሲል ያልተካተቱ ሥፍራዎች መካተታቸውን ጠቅሰው፤ ለዩኔስኮ የቀረበው ሰነድ ሲፀድቅ የፓርኩን ዓለም አቀፍ እውቅና ያሳድጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም