ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባለፈ አብሮነትና ወንድማማችነትን ያጎለብታሉ - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባለፈ አብሮነትና ወንድማማችነትን ያጎለብታሉ
ወልቂጤ ፤የካቲት 19/2018(ኢዜአ) :- ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባለፈ አብሮነትና ወንድማማችነትን ለማጎልበት እንደሚያስችሉ ተመላከተ።
በወልቂጤ ከተማ ለተከታታይ 10 ቀናት ሲካሄድ የቆየው 3ኛው የክልል አቀፍ ሻምፒዮናና የባህል ስፖርቶች ውድድር ፌስቲቫል ተጠናቋል፡፡
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሶ፤ በወቅቱ እንዳሉት ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባለፈ አብሮነትና ወንድማማችነትን ያጎለብታሉ።
በ17 ዘርፎች የተካሔደው ስፖርታዊ ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር የሚችሉ ስፖርተኞች የተለዩበት እንደሆነም ገልፀዋል።
ስፖርታዊ ውድድሩ በዋናነትም በዘርፉ የወጣቶችን ተሰጥኦ ለመለየት እገዛው የጎላ እንደነበርም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት በዘርፉ የሚፈገለውን ውጤት ለማምጣት የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶችን ከመገንባት ባሻገር ስፖርታዊ ጨዋነትን የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፣ መርሃ ግብሩ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጎልበት በተሻለ መንገድ አንድነትን ለመፍጠር ያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ስፖርታዊ ውድድሩ በአካባቢው ላይ መነቃቃትን የፈጠረ ሲሆን የባሕል እሴቶችንም ለማስተዋወቅ ትልቅ እገዛ አድርጓል ነው ያሉት።
ታዳጊ ወጣቶችን ለማፍራት የተከናወኑት ተግባራት አዳዲስ እና ተተኪ ስፖርተኞች የተገኙበት መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ትምህርት ስልጠና ባለሙያ አቶ ባዘዘው ደምሴ ናቸው ።
በዞኑ በተዘጋጀው የውድድር መርሃ ገብር ላይ በ17 ዓይነት የውድድር ዘርፎች ተወዳዳሪዎችን ማሳተፍ መቻሉን ጠቅሰው ይህም መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ያመላክታል ብለዋል።
የጠንባሮ ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ፅህፈት ቤት የስፖርት ተሳትፎና ውድድር ቡድን መሪ አቶ አባይነህ ጎበዜ በበኩላቸው፤ በክልሉ በስፖርት ዘርፍ የተጀመረውን ሥራ ለማጠናከር እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎችና የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን በስፖርታዊ ውድድሩ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ስፖርተኞች የሜዳሊያ፣ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።