ቀጥታ፡

በሁሉም የልማት መስኮች የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ሀገራዊ ዕድገትን ያፋጠኑ ስኬቶች ተመዝግበዋል

ቦንጋ/ሚዛን፤የካቲት19/2018 (ኢዜአ)፡-ብልጽግና ፓርቲ በሁሉም የልማት መስኮች የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ሀገራዊ ዕድገትን የሚያፋጥኑ የልማት ስኬቶችን በተግባር ማስመዝገቡ ተገለጸ።

ፓርቲው ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመወዳደሪያ ምልክቱ የሆነውን የስንዴ ነዶ እና ማኒፌስቶውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን እና ቦንጋ ከተሞች ዛሬ ለህዝብና ለደጋፊዎቹ አስተዋውቋል።

በቦንጋ ከተማ በተካሄደ መድረክ ላይ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፣ ብልጽግና ባለፉት ዓመታት እዳን ወደ ምንዳ በመቀየር በፈጠራና በፍጥነት እሳቤ ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየተጋ ያለ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል። 

ፓርቲው የተከተለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕሳቤ ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት ድህነት ወጥታት በልማት ተምሳሌት  ወደምትሆንበት ለመሸጋገር የሚያስችላት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በፓርቲው መሪነት ባለፉት ዓመታት በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውንና ይህም ተጠናከሮ መቀጠሉን ነው የተናገሩት።

በማህበራዊ ዘርፍም ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን በማከናወን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ትችሏል ብለዋል።

በዞኑ ሰፊ የልማት ሀብት ቢኖርም ትኩረት ባለመሰጠቱ ህዝቡ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል ያሉት አስተዳዳሪው፣ በፓርቲው መሪነት በዞኑ ልማትን ለማፋጠን በተሰራው ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት የሆነው የስንዴ ነዶ የአብሮነት፣ የጥንካሬ፣ የአንድነትና በምግብ ራስን የመቻል መሆኑን ጠቁመው፣ ፓርቲውን መምረጥ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ማስቀጠል ነው ብለዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የካፋ ዞን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጥናፉ ሀይሌ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ብልፅግና ፓርቲ እንደሀገር የገጠሙ ስብራቶችን በመጠገንና ልማትን በማስቀጠል ዜጎችን ተጠቀሚ እያደረገ ይገኛል።

በካፋ ዞን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስመዝገብ በትኩረት በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት እየመጣ ነው ያሉት ሀላፊው፣ በዚህም የዞኑ ነዋሪዎች ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መጥቷል ብለዋል።

ዞኑ በልማት ወደኋላ ቀርቶ እንደነበረ አቶ አጥናፉ አስታውሰው፣ በፓርቲው መሪነት ይህን ለመቀየር የተወሰደ እርምጃ ህዝብን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተመሳሳይ ዜና በሚዛን አማን ከተማ በተከሄደ መድረክ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን እንዳሉት ፓርቲው የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ሀገራዊ ዕድገትን የሚያፋጥኑ የልማት ሥራዎችን በተጨባጭ እያከናወነ ይገኛል።

ምርጫ ለአንድ ሀገር ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ምሰሶ በመሆኑ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በፓርቲው መሪነት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችና አዳዲስ እሳቤዎች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የልማት ተምሳሌት የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ብልጽግና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡና ሀገራዊ ዕድገትን የሚያፋጥኑ የልማት ሥራዎችን በተጨባጭ ያስመዘገበና ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ዓልሞ የሚሰራ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ዞኑ ከሀገራዊ ለውጡ ትሩፋት ተጠቃሚ መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ በብዝሃ ኢኮኖሚ እይታ የተገነባው የደንቢ ኢኮ ሎጅ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ፓርቲው ድህነትን ለማሸነፍ በግብርና ዘርፍ የጀመራቸው ኢኒሼቲቮች ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበባቸው በመሆኑ የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ ነው ብለዋል። 

ብልጽግና የኢኮኖሚ አማራጭ መፍጠሩ በአካባቢያችን ያሉ አንጡራ ሀብቶችን አውጥቶ ለመጠቀም አስችሏል ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የቤንች ሸኮ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደግፌ ኩድን ናቸው።

በቦንጋና በሚዛን አማን ከተማ በተካሄዱ መድረኮች የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።

 

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም