ኢትዮጵያ የገነባችው አስተማማኝ ሠራዊት በቀጣናው ያላትን የሠላም አለኝታነት የሚያጸና ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የገነባችው አስተማማኝ ሠራዊት በቀጣናው ያላትን የሠላም አለኝታነት የሚያጸና ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የገነባችው አስተማማኝ ሠራዊት በቀጣናው ያላትን የሠላም አለኝታነት የሚያጸና መሆኑን የቀድሞው የአየር ወለድ አዛዥና ወደር የሌለው የኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ሜዳይ ተሸላሚ ብርጋዴር ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ገለጹ፡፡
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በተከበረበት ወቅት፣ ከኢትዮጵያ ባለፈ የቀጣናውንና የአፍሪካን ነጻነትና ሰላም ዛሬም እንደትናንቱ የሚያስከብር አስተማማኝ ኤሊት ፎርስ ተገንብቷል ብለዋል፡፡
የሠራዊቱ የተሟላ ዝግጁነት በድፍን አፍሪካ ሰላም እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቀጣናው ላሉ ሀገራትም አለኝታና መከታ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የቀድሞው የአየር ወለድ አዛዥና ወደር የሌለው የኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ሜዳይ ተሸላሚ ብርጋዴር ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ወታደራዊ ሳይንስን፣ ስነ-ልቦናዊ ግንባታን እና የአካል ብቃትን መሠረት አድርጎ የተገነባ ሠራዊት ለሀገር ህልውና ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ስልጠና የድል በር መክፈቻ ቁልፍ ነው ያሉት ብርጋዴር ጀነራሉ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ሠራዊት ጥራት ያለው፣ በሁሉም መልኩ የተዘጋጀ አስተማማኝ ኃይል መሆኑን ገልጸዋል።
በ65ኛው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የምስረታ በዓል የተመለከቱት የሠራዊቱ ትርኢትም በሁኔታዎች የማይበገር ወሳኝ ኃይል መገንባቱን ያሳየ ነው ብለዋል።
"በሕይወት ኖሬ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዚህ መልኩ ተገንብቶ በማየቴ እንደገና እንደተወለድኩ ነው የቆጠርኩት" ሲሉም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገነባችው ኃይል የራሷን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ የአካባቢው ሀገራት ጭምር የሚታመኑበትና ዋስትና የሚሆናቸው ኃይል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሠራዊት ቁመና እና ጥንካሬ ያደነቁት ብርጋዴር ጀኔራሉ፥ ይህም ሀገራችን በቀጣናው ያላትን የሠላም አለኝታነት የሚያጸና መሆኑን ገልጸዋል።
ሠራዊቱ ሁሉንም አቀፍ እውቀትና ዘመናዊ ትጥቅ የታጠቀ በመሆኑ በአየር፣ በባህር፣ በየብስ እንዲሁም በየትኛውም አውድና የመሬት ገፅ ድል አብሳሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ አክለውም ኢትየጵያ ተግባርና ኃላፊነቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ በሥነ-ምግባር የታነጸና ከራሷ አልፎ ለአፍሪካውያን ሠላም ዋስትና የሚሆን ሠራዊት መገንባቷን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሶማሌ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ በባህር ላይ የሚያጋጥሙ ሽብሮችን የሚያስቀር ኤሊት ፎርስ መገንባቱን መግለጻቸው ይታወቃል።
ተቋም የምንገነባው፣ ኤሊት ፎርስ የምንገነባው፤ በቀጣናችን ውጊያና ሽብር እንዳይፈጠር ነው፤ ሲፈጠርም በአጠረ ጊዜ ለመቋጨት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ይህን አይነት ተቋም በመገንባቷ የምስራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ሀገራት እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።