በለውጡ መንግስት የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች የጌዴኦ ዞን ህዝብን ተጠቃሚ አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በለውጡ መንግስት የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች የጌዴኦ ዞን ህዝብን ተጠቃሚ አድርገዋል
ዲላ፣ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡-በጌዴኦ ዞን ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት በተጨባጥ ያረጋገጡ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
ብልጽግና ፓርቲ "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ ማኒፌስቶውንና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱ የሆነውን የስንዴ ነዶ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ለህዝብና ለፓርቲው ደጋፊዎች አስተዋውቋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት ፓርቲው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምን ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሸጋጋር ተግቶ እየሰራ ነው።
በዚህም የጌዴኦ ህዝብ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት አመርቂ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ በቡና ልማት በሄክታር እስከ 19 ኩንታል በማግኝት ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው ቡና ከ40 ሺህ ቶን በላይ መድረሱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በእንሰትና ፍራፍሬ ልማትም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መቻሉን አንስተው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፓርቲው መሪነት በዞኑ የመጡ ድሎችን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የዞኑ ህዝብም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ምርጫው ስላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነጻ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
በከተማው ባለፉት አምስት ዓመታት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ጨምሮ ከ252 በላይ የልማት ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት በማብቃት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መሰጠቱን ያነሱት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) ናቸው።
በተለይ በከተማው ሁሉንም የመንግስት አገልግሎት በማዘመንና ዲጂታል በማድረግ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የህዝብን የዘመናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በተሰራው ስራ ውጤት መመዝገቡን ነው ያስታወቁት።
ፓርቲው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝብን ይሁንታ ካገኘ እነዚህን የተመዘገቡ ውጤቶች በማጠናከር ለላቀ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጌዴኦ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፍት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው ጠቅላላ ምርጫው የፓርቲው የመወዳደሪያ ምልክት የስንዴ ነዶ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻልና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በገጠርና በከተማ በተለያዩ መስኮች እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና በርካታ የፓርቲው ደጋፊዎች ተገኝተዋል።