ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተገኝቷል

አሶሳ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መገኘቱን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በኮሚሽኑ አማካኝነት በአቡራሞ ወረዳ የለማ ሰብል ተሰብስቧል።

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሐመድ አብዱላዚዝ፣ እንዳሉት በ2016/17 የምርት ዘመን ለሰብዓዊ ድጋፍ ታስቦ በውስን አካባቢዎች የተጀመረው የሰብል ልማት አበረታች ውጤት ተገኝቶበታል።


 

በዘንድሮው ዓመት በክልሉ 1 ሺህ 804 ሄክታር ማሳ ላይ በለማው የበቆሎ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎች ሰብሎች እስከአሁን ድረስ 36 ሺህ 211 ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ ከ43 ሺህ  ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፥ የምርት አሰባሰብ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ዕቅዱ ሙሉ ለሙሉ እንደሚሳካ ጠቁመዋል።

የክልሉ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን በራሱ አቅም በክልሉ አቡራሞ እና ሆሞሻ ወረዳዎች ላይ ካለማው ማሳ 2 ሺህ 200 በላይ ኩንታል ምርት መሰብሰቡንም ተናግረዋል።

የተሰበሰበው ምርት የውጪ እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያግዝና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።

ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ምርቱም ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል።

በቀጣይም በክልሉ የሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎችን በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እና ከተረጂነት ለመላቀቅ የተያዘውን የዜሮ ፕርሰንት ሀገራዊ ግብ ለማሳካት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም