ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን የሚያሳድጉ የውሃ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ባህር ዳር ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን የሚያሳድጉ የውሃ ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ በተከናወኑ የውሃ ተቋማት ግንባታና ጥገና ከ170 ሺህ በላይ ዜጎች የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል።

የውሃ ተቋማቱ በተለይም በገጠርና በከተማ የሚገኙ እናቶችንና ሕፃናትን ከእንግልት መታደግ ችለዋል።

የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጥላሁን ሽመልስ ለኢዜአ እንዳሉት በገጠርና ከተሞች የንፁህ መጠጥ ውሃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ እየተከናወነ ነው።

በተያዘው በጀት ዓመት ከሁለት ሺህ በላይ አነስተኛ የውሃ ተቋማትን ለመገንባት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አመልክተዋል።

ባለፉት ሰባት ወራት  ከሁለት ሺህ በላይ የውሃ ተቋማትን ወደ ግንባታ ማስገባት የተቻለ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የ306ቱን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን አብራርተዋል።

እንዲሁም የ55 ከፍተኛ የውሃ ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣  ከእነዚህ ውስጥ 17 የሚሆኑት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ነው ያሉት።

የውሃ ተቋማቱ ከ170 ሺህ በላይ ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን ገልጸው የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን እየተከናወኑ ያሉ ግንባታዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በክልሉ ለብልሽት የተዳረጉ ከ13 ሺህ በላይ የውሃ ተቋማት በሕብረተሰብ ተሳትፎ ተጠግነው ለአገልግሎት በቅተዋል።

የውሃ ተቋማቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥም አደረጃጀት በመፍጠር የጥበቃና የእንክብካቤ ስራ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተው በቀሪ ወራትም ግንባታቸው የተጀመሩ የውሃ ተቋማትን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ በለሳ ወረዳ ነዋሪ ማሪቱ በላይነህ በአቅራቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ባለመኖሩ ውሃ ፍለጋ ረጅም መንገድ በመጓዝ እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

በአቅራቢያቸው ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የውሃ ፕሮጀክት የቀደመ ችግራቸውን በመፍታቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ተገንብቶ አገልግሎት የጀመረው የጋብላ ውሀ ፕሮጀክት የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግራችንን የፈታ ነው ያሉት ደግሞ በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ጋብላ ከተማ ነዋሪ ግርማ ደግሰው ናቸው።

ሌላኛዋ በዚሁ ወረዳ ጠረፍ ወርቅ ቀበሌ ነዋሪ  ፋሲካ አንተነህ እንዳሉት፤ በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋም ለአገልግሎት መብቃቱ ውሃ ለማግኘት ያደርጉት የነበረውን ረጅም ጉዞ እንዳስቀረላቸው ገልፀዋል።

በክልሉ አሁን ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከ77 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን ይህን ለማሳደግ የተለያዩ የውሃ ተቋማት ግንባታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም