ብልጽግና ፓርቲ አካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ይተጋል -የፓርቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ አካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ይተጋል -የፓርቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች
ባህርዳር/ጎንደር/ገንዳ ውሃ/ደብረ ማርቆስ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ አካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ እየተጋ መሆኑን የፓርቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
ፓርቲው "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ ማኒፌስቶውንና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱን በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ አስተዋውቋል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ ፓርቲው ከተማዋን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ በኮሪደር ልማት፣ በስማርት ሲቲና በአረንጓዴ ልማት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
አካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ እየተጋ ያለ ፓርቲ መሆኑንም አንስተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞላ ሁሴን በበኩላቸው፣ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ልማትን በመስራት ለዘንድሮው ምርጫ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው ምርጫውን ለማሸነፍና የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠን በተሻሉ ሀሳቦች ጠንክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ አባላትና ደጋፊዎች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን በትጋት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፤ ፓርቲው ከተሞችን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የጀመራቸው ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
ለዘመናት ተረስቶ የነበረውን የፋሲል ግንብ ቅርስ በማደስ ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ማድረጉን ለአብነት በማንሳት።
በፓርቲው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተስፋ መኮንን በበኩላቸው፣ ፓርቲው ያልተማከለና አካታች ሥርዓት ለመገንባት እየተጋ መሆኑን ገልጸው አባላት ለስኬቱ እንዲተጉ ጠይቀዋል።
በፓርቲው የምዕራብ ጎንደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዳለው ማሩ፣ ፓርቲው የከተማና የገጠር ትስስርን በማጠናከር የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መልካሙ ሽባባው፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲው በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
ፓርቲው በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የገባውን ቃል በተግባር ማሳካቱ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።
በከተሞቹ በተካሄደው የማስተዋወቂያ መድረክ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች የተገኙ ሲሆን የፓርቲው የመወዳደሪያ ምልክት የስንዴ ነዶ መሆኑንም አስተዋውቋል።