ኮሎምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር አድማስ ለማስፋት ትሻለች - አምባሳደር ዮሶን አርካዲዮ ሜኔስ ኮፔቴ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሎምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር አድማስ ለማስፋት ትሻለች - አምባሳደር ዮሶን አርካዲዮ ሜኔስ ኮፔቴ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ ኮሎምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር በታሪክ እና ባህል ያላትን ትስስር በሌሎች መስኮችም የማስፋት ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የኮሎምቢያ አምባሳደር ዮሶን አርካዲዮ ሜኔስ ኮፔቴ ገለጹ።
አምባሳደር ዮሶን ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ ትስስር እንዳላቸው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
የአድዋ ድል በኮሎምቢያ ለሚኖሩ የአፍሮ-ካሪቢያን ዝርያ ላላቸው ዜጎች የክብር እና የተነሳሽነት ምንጭ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአድዋ ድል የሰብዓዊነት እናት፣ የታጋይነት እና አይበገሬነት ምልክት ሆናለች ሲሉም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተካሄዱ የፀረ-ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴዎች ቁልፍ ሚና አላት ብለዋል።
የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው የኮሎምቢያ ዜጎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ትስስር ለሀገራቱ የባህል ትብብር የጠለቀ እንዲሆን አድርጎታልም ነው ያሉት አምባሳደሩ።
አምባሳደር ዬሰን የኮሎምቢያ እና ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን አንስተው በተለይም ሀገራቱ በቡና ዘርፍ የቴክኒክ ልውውጦች እና የጋራ ውይይቶችን በቋሚነት እያደረጉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ምርት ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመከላከል ሀገራቱ በትብብር እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል።
ቡና ለሁለቱም ሀገራት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው ለዜጎች የኑሮ መሻሻል እና የገቢ እድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
በሌላ በኩል አምባሳደሩ የአዲስ አበባን ፈጣን ለውጥ በማድነቅ ከኮሎምቢያ መዲና ቦጎታ ጋር ያላትን ትብብር አንስተዋል።
ቦጎታ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የከተማ ሪፎርሞች ውስጥ ማለፏን አውስተው ሁለቱ ከተሞች ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የከተማ ልማትን ለማስፋት የልምድ ልውውጦችን እያደረጉ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ኮሎምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም ጨምረው አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1947 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኮሎምቢያ በነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኤምባሲ ዳግም መክፈቷ የሚታወስ ሲሆን ይህም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል።