በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን የማስፋት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን የማስፋት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ሆሳዕና ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን የማስፋት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በክልሉ የመንገዶች አስተዳደር የሆሳዕና ዲስትሪክት የተገነባው የማሬ -አቡና -መሰና -ጃጁራ የ30 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የክልሉ መንግሥት የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራትን እውን የማድረግ ስራን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ልማት እንዲገቡ ይደረጋል
በተለይ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን የማስፋት ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል ፈጣን እድገትን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው መንገድ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ መሰረተ ልማቱን በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑርዬ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተመረቀው የ30 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ በርካታ እድሎችን ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የተገነባው መንገድ ከምባታ ዞንን ከሀዲያ ዞን ጋር በሚያገናኙ በ11 ቀበሌያት በኩል በማለፍ ወደ 262 ሺህ የሚጠጋ ቁጥር ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የመንገዱ ግንባታ ከ 173 ሚሊዮን 963 ሺህ ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትም ገልፀዋል፡፡
የመንገድ መሰረተ ልማቱ መጠናቀቅ በአካባቢው የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ እንደሚረዳ የተናገሩት ደግሞ የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ ናቸው፡፡
አካባቢው በግብርናው ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም የመንገዱ ግንባታ ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።
በአካባቢው በነበረው የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ያመረቱትን ምርት ለገበያ ለማቅረብ ይቸገሩ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ በሀዲያ ዞን በሶሮ ወረዳ የ2ኛ በናራ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ገበየሁ ሐይሉ ናቸው፡፡
ወላድ እናቶችንና የጤና እክል የገጠማቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ ይገጥም የነበረውን ችግር ከማቃለል አንፃርም የመንገዱ ግንባታ ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚኖሩው ነው የጠቀሱት።
በመርሐ ግብሩ የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡