የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የገበያ ትስስርና ዘላቂ የግብዓት አቅርቦትን እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የገበያ ትስስርና ዘላቂ የግብዓት አቅርቦትን እየፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለምርቶቻቸው የገበያ ትስስርና ዘላቂ የግብዓት አቅርቦት እየፈጠረላቸው መሆኑን አምራቾች ገለጹ።
የኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በበኩሉ፥ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቋማዊ ቅንጅትን በማጠናከር በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን የሚፈታ ምህዳር መፍጠሩን አስታውቋል።
መንግሥት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ አንዱ የብዝኃ ዕድገት ምሰሶ አድርጓል።
በተለይም በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች በተኪ ምርት ላይ እንዲያተኩሩና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን እንዲያሳድጉ መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።
ለዚህም በዘርፉ ያሉ መዋቅራዊ ማነቆዎችን በመፍታት እመርታ ለማምጣት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ትግበራ ገብቶ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ ነው
ኢዜአ ያነጋገራቸው አምራቾች እንደገለጹት፣ ንቅናቄው የገበያ ትስስርን ለመፍጠር፣ የግብዓት አቅርቦትን ለማመቻቸትና ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
የአሸናፊና ይርጋለም ብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ህብረት ሽርክና ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አሸናፊ ኃይለጊዮርጊስ፥ ማህበሩ ከውጭ የሚገቡ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽኖችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየሰራ ነው ብለዋል።
ንቅናቄው አምራቾችን ከመንግሥትና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በማገናኘት የግብዓት አቅርቦት ችግሮች እንዲፈቱ መንገድ መክፈቱን ጠቅሰዋል።
የዌላንድ ኢንዱስትሪ የፕሮጀክት ማናጀር ሊዲያ ተስፋዬ፥ ንቅናቄው ለኤሌክትሪክ ገጠማ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶቻቸውን በቀላሉ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ እንደረዳቸው አንስተዋል።
በፋሲል ታሪኩ የቤትና ቢሮ እቃዎች ማምረቻ ባለሙያ የሆኑት ወንድምነህ አብየ፣ በሀገር ውስጥ የተመረቱ የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ ማሽነሪዎች ማግኘት መቻላቸው ለስራቸው ትልቅ እገዛ ማድረጉን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃገማ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ንቅናቄው ከመጀመሩ በፊት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በግብዓት፣ በፋይናንስና በአሰራር ጉድለቶች ምክንያት ዝቅተኛ ነበር።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቋማዊ ቅንጅትን በማጠናከር በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን የሚፈታ ምህዳር ፈጥሯል ብለዋል።
የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 66 ነጥብ 3 በመቶ ማደጉን፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የሚገመቱ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ጠቅሰዋል።