በዞኑ ለዘንድሮ የበልግ እርሻ የሚውል ከ892 ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ለዘንድሮ የበልግ እርሻ የሚውል ከ892 ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል
ነገሌ ቦረና ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ ቦረና ዞን ለዘንድሮ የበልግ እርሻ የሚውል ከ892 ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወጪን ለመቀነስ አግዞናል- በምሥራቅ ጎጃም አርሶ አደሮች
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ኩልሌ ሸና እንዳሉት፤ ከፊል አርብቶ አደሩ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በመሆኑም ለዘንድሮ የበልግ እርሻ የሚውል አንድ ሚሊዮን ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከፊል አርብቶ አደሮችን በማሳተፍ 892 ሺህ 934 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት መቻሉን አስረድተዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያው በዘንድሮው ዓመት በበልግ እርሻ ለሚለማው ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በግብዓትነት እንደሚውል ገልጸዋል።
በዞኑ በስፋት የሚካሄደው የእንስሳት እርባታ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው ይህን አቅም ለመጠቀም ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ዝግጅቱ ከፋብሪካ የሚገኘውን ማዳበሪያ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ እስከ ሶስት ዓመት ከፍተኛ ምርት ለማግኘት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ በተጨማሪ ለበልግ እርሻ የሚውል ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ደርሶ ስርጭት እየተካሄደ መሆኑን አክለዋል።
የበልግ እርሻ ስራን ለማቀላጠፍ በርካታ የእርሻ ትራክተሮች ወደ አካባቢው እየገቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዞኑ በበልግ እርሻ ከሚለማው 178 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱንም አንስተዋል።
ባለፈው መኸር ወቅት ያለሙት የስንዴ ሰብል በዝናብ እጥረትና በግብአት አጠቃቀም ጉድለት ውጤታማ ባለመሆኑ እሱን ለማካካስ እየሰራሁ ነው ያሉት በዞኑ ሊበን ወረዳ የመኤሳ ዳሎሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እስማኤል ማሊማ ናቸው።
ለዚህም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ሊበን ወረዳ የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪ አብዲ ኑር፤ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በሰብል ልማት በመሳተፍ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል።
በዘንድሮ ዓመትም የተፈጥሮና የፋብሪካ ማዳበሪያ በማመጣጠን እና የተሻሻለ የግብርና አሰራር በመከተል ከበልግ አዝመራ የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በምስራቅ ቦረና ዞን ከመጋቢት 15 እስከ ሚያዝያ መጨረሻ የዝናብና የበልግ አዝመራ ወቅት ነው።