በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት 668 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት 668 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ ገብተዋል
አዳማ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በማስፋት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰራው ሥራ 668 የውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ እንደገቡ የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮ ሃላፊዋ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በማስፋት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በዚህም አዳዲስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች ተበላሽተው የነበሩ የውሃ ፕሮጀክቶችን የመጠገን ሥራ መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመትም 375ሺህ ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ 668 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ተበላሽተው ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ 1ሺህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችንም በመጠገን የተቋረጠውን አገልግሎት ዳግም ማስጀመር ተችሏል ብለዋል።
ለብዙ ጊዜ ግንባታቸው የተጓተተና የህዝብ ቅሬታ ምንጭ የሆኑ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑንም ኢንጂነር ሚሊዮን አመልክተዋል።
እስካሁንም የባሌ ሮቤ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ መጠናቀቁን ገልጸው በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱን ከነባር መስመሮች ጋር የማገናኘት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በተመሳሳይ የወሊሶ ከተማ የውሃ ፕሮጀክት ግንባታና የመስመር ዝርጋታ ከሁለት ቀበሌዎች በስተቀር መጠናቀቁን ጠቁመው የሞጆ አዳማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም ተጠናቆ በከፊል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል።
በቀጣይም አፈጻጸማቸው ከ85 በመቶ በላይ የደረሱ ትላልቅ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራን በማጠናከር በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የውሃ ፕሮጀክቶችን ሙሉ ለሙሉ አጠናቀን ለአገልግሎት ለማብቃት የተጀመረው ርብርብ ይጠናከራል ብለዋል።