የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞችን መረጃ የሚያዘምን ፕሮጀክት ማስጀመሩን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞችን መረጃ የሚያዘምን ፕሮጀክት ማስጀመሩን አስታወቀ
አዲስ አበባ ፤የካቲት 18 /2018 (ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞች መረጃ የሚያዘምን የፕሮጀክት ሙከራ ትግበራ ማስጀመሩን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የደንበኞች አገልግሎቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሥርዓት የተደገፉ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውንም በባለሥልጣኑ የአገልግሎት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አርጋው እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተወካይና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ገረመው ሳህሌ በጋራ ሰጥተዋል።
አቶ ሞገስ አርጋው በዚህ ወቅት፤ የደንበኞችን የውሃ አቅርቦት አገልግሎቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስተሳሰር የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የደንበኞች መረጃ ማዘመን ፕሮጀክት ትግበራም የቢል፣ ማህደርና የመሬት መረጃዎችን በማጣጣም ዘመናዊ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና የውሃ ብክነትን የሚቀንስ አገልግሎቶችን ለመስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማም የተሟላ፤ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ በማደራጀት አሠራርን ዲጂታላይዝ በማድረግ የተቀላጠፈ የመስመር ላይ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተወካይና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ገረመው ሳህሌ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የውሃ አገልግሎቶችን የሚያሳልጥ የስማርት ሲቲ ግንባታ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱም የውሃና ሳኒቴሽን ሥርዓትን በማዘመን የባለስልጣኑን ተለምዷዊ አገልግሎት አሰጣጥ መቀየር የሚስችል ምኅዳር የሚፈጥርና ዘላቂነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞች መረጃ የሚያዘምነው ፕሮጀክትም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በይፋ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይም ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚሰራ ተጠቁሟል።