ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የገነነችበት ዲፕሎማሲና የስትራቴጂካዊ እይታ ስኬት!

(በሙሴ መለስ)

ባለፉት ጥቂት ወራት በኢትዮጵያ የሚደረጉ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች፣ ታላላቅ ዲፕሎማቶች ጉብኝቶች እና የግንኙነት መድረኮች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላት ተሳትፎ እየጨመረ የዲፕሎማሲ ስኬቷም የተጽዕኖ ደረጃው እያደገ ስለመምጣቱ የሚያሳዩ ናቸው።

የዓለም መሪዎች ከስትራቴጂካዊ አጋርነት እስከ ቀጣናዊ ትብብር የዘለቀ ግንኙነትን ዓላማ ያደረጉ ጉብኝቶችን በአፍሪካ መዲና ኢትዮጵያ አድርገዋል። ጉብኝቶቹ የኢትዮጵያን ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እና የዲፕሎማሲ አቅም የሚያሳዩም ናቸው።

መሪዎቹ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ያደረጓቸው የሁለትዮሽ ውይይቶች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ትስስርን ማጎልበት እና በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ጥረቶች እንዲሁም የጋራ የሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን በትብብር መፍታት ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ የልብ ምት ናት። አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ መሆኗ የዓለም መሪዎች ትኩረት እንዲያርፍባት አድርጓል። ጉብኝቶቹ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ሰፊ በሆኑ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ እያደገ ያለውን ተሰሚነቷን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው።

ፈተናዎች በበዙበት የአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ በሰላም ግንባታ፣ ኢኮኖሚ ትብብር እና አህጉራዊ ትስስር ገንቢ ሚና እንደምትጫወት እና አስፈላጊነቷ ወሳኝ እንደሆነ ከመሪዎቹ ንግግር መረዳት ይቻላል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ሃገራችንን ከጎበኙ የውጭ ሃገራት መሪዎች መካከል ባለፈው ሣምንት የመጡት የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን አንዱ ናቸው።

ኤርዶዋን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።ቱርኪዬ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት የረጅም ጊዜ ትብብር ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥ እና አጋርነቷን ማጠናከር እንደምትሻ ተናግረዋል።

ኤርዶዋን ኢትዮጵያ በቀጣናው ስላላት ሚና በማንሳት ዓለም ፊቱን ወደ አፍሪካ ቀንድ ባዞረበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ጸንቶ የቆየ የሀገረ መንግስት መዋቅር እና ተምሳሌታዊ አስተዳደር የበለጠ አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ጉብኝቱ መልካም ውጤቶችን ይዞ እንደሚመጣና ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሙሉ እምነት አለኝ ማለታቸውም አይዘነጋም።

በዓለም ከፍተኛውን የህዝብ ቁጥር የያዘችው ህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።

ሞዲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብስባ ላይ በመገኘት በጥልቅ ስሜት ባደረጉት ታሪካዊ ንግግርም ህንድ እና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ወዳጅነት እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዳላቸው አንስተዋል።

የህንድ ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰው ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በግብርና፣ ጨርቃ ጨርቅና ማኑፋክቸሪንግን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራታቸውን አመልክተዋል።

ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ስትራቴካዊ አጋርነት ምዕራፍ ለማሸጋገር መወሰኗን ገልጸው ይህም ኢኮኖሚ፣ ንግድ ፣ ኢንቨስመንት፣ ቴክኖሎጂ፣ ማዕድን፣ አረንጓዴ ኢነርጂ እና ኢኖቬሽንን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ህንድን ታማኝ አጋር በማድረጓ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ናሬንድራ ሞዲ ሀገራቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር አበክራ እንደምትሰራ መናገራቸው ሌላው የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ የሚያመለክት ሲሆን ሞዲ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ እና ዘመናዊ ህልሞችን አጣምራ መያዟ በአይበገሬነት እና በጽናት መንፈስ እንድትቀጥል አድርጓታል ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም ጥንታዊ ስልጣኔዎች ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት መሆኗን ያነሱት የጥንካሬ፣ የአይበገሬነት፣ የኩራት እና የለውጥ ምልክት ናት ሲሉ መግለጻቸውም አይዘነጋም።

በዚሁ ዓመት ታህሳስ ወር ላይ አዲስ አበባን የጎበኙት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያን የልማት ስራዎች ያደነቁ ሲሆን ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በልማቱ ዘርፍ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።

ቻይና ለቀጣናዊ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽግና ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደምትስራ በመግለጽም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት(all-weather strategic partnership) ይበልጥ ለማጎልበት በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።

የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፈር ላንዳውና በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ዕዝ (አፍሪኮም) ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ያረጋገጡት ነገር ቢኖር የኢትዮጵያን ቀጣናዊና ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ነበር።

በወቅቱ ክርስቶፈር ላንዳው እና ልዑካቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተወያዩ ሲሆን ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኤክስፖም ጎብኝቷል። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆየውን አጋርነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን በመግለጽ አሜሪካ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደምትፈልግም አመልክተዋል።

የደቡብ ምስራቅ እስያዊቷ ሀገር ሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ አዲስ አበባን የጎበኙት በህዳር ወር 2018 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሁለትዮሽ ውይይቶችን ያደረጉ ሲሆን በአፍሪካ የመጀመሪያቸውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በኢትዮጵያ አዲስ አበባ በማድረጋቸው ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሲንጋፖር በአዲስ አበባ ኤምባሲ ለመክፈት መወሰኗን በደስታ እንደተቀበሉት በወቅቱ ዎንግ ገልጸውም ነበር። 

የኤምባሲው መከፈት ሲንጋፖር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ህብረት እና ከመላው አፍሪካ ጋር ቁልፍ ትስስር መፍጠሪያ ሆኖ እንደሚያገለግልም አመልክተዋል።

ሲንጋፖርና ኢትዮጵያ የየቀጣናቸው መግቢያ በር ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራቱ ያላቸውን አጋርነት የበለጠ በማጠናከር ዜጎችን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ድልድይ በደቡብ ምስራቅ እስያ እና አፍሪካ መካከል እየገነቡ ነው ብለዋል።

ከእስያ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ስንመለስም የኬንያውን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም ባደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የመሪነት ሚና በማድነቅ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ላይ ገንቢ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ አንስተዋል።ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ለማጎልበት እንደምትሻም ገልጸዋል።

በአውሮፓ የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆአን ዋድፑልም በጥር ወር ባደረጉት የኢትዮጵያ ጉብኝት ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት ያደነቁት ሚኒስትሩ፤ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት የጀርመን ኩባንያዎች በግንባታው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ፣ ኮመንዌልዝ እና የልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ይቬት ኩፐር፣ የኖርዌይ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪያስ ክራቪክ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒትር ዴኤታ ኩኒሚትሱ አያኖ እና የሌሎች ሃገራት መሪዎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።

 

በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የተደረጉ የከፍተኛ ደረጃ ጉብኝቶች ጉብኝት ብቻ ሆነው ያለፉም ብቻ አይደሉም። ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ያላትን ተሰሚነትም የሚያሳዩ ናቸው።

ህንድ እና ቱርኪዬን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ምዕራፍ አሸጋግረዋል።

የዓለም ሀገራት መሪዎቹ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን በመፍታት ረገድ ያላትን ወሳኝ ሚና አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በደቡብ ደቡብ ትብብር ያላት ስትራቴጂካዊ ሚናም የተነሳ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ የትብብር፣ የሰላም፣ የጋራ አጋርነት እና ዘላቂ ልማት ማዕከል መሆኗን የሚያሳይ ነው።

ጉብኝቶቹ እንግዳን ተቀብሎ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን ከማድረግ ባለፈ ኢትዮጵያ በቀጣናውና በዓለም የዲፕሎማሲ ውስጥ ያላትን ቦታ አጉልተው ያመላከቱ የስኬት መገለጫዎችም ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም