የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን የግጭት ማእከል የማድረግ ፍላጎት ካላቸው ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን የግጭት ማእከል የማድረግ ፍላጎት ካላቸው ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ ፤የካቲት 18 /2018 (ኢዜአ)፡- የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን የግጭት ማእከል የማድረግ ፍላጎት ካላቸው ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ገለጸ።
የክልሉ ህዝብ የሰላም እና የልማት አጀንዳዎችን ይዞ መቀጠል እንደሚፈልግም አስታውቀዋል።
በትግራይ አሁን ላይ ያለውን አሁናዊ ወቅታዊ ሁኔታ እና አጠቃላይ የህዝቡን ፍላጎት በተመለከተ ኢዜአ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ገብረጊዮርጊስ ግደይን አነጋግሯል።
በማብራሪያቸውም የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ አፍኖ ከመያዝ ባለፈ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የጦርነት አጀንዳ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለውጥ ፈላጊ በመሆን በሰላም የመኖር ጥያቄ እያነሳ ቢሆንም በቡድኖ ታፍኖ ስቃይና እንግልት እየደረሰበት ስለመሆኑ አንስተዋል።
የህወሃት ቡድን ከክልሉ አልፎ ኢትዮጵያን የግጭት ማእከል የማድረግ ፍላጎት ካላቸው ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ቡድኑ በትግራይ ክልል ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ክልሉ በአዲስ እሳቤ እና በወጣቶች እንዳይመራ ያረጀ አስተሳሰብ ይዞ በጥፋቱ ቀጥሎበታል ሲሉ ተናግረዋል።
የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን የግጭት ማእከል የማድረግ እቅድ ካላቸው ጠላቶች ጋር ግንባር በመፍጠር የሚያደርገውን የጥፋት እንቅስቃሴም በጋራ ቆመን መመከት ይገባናል ሲሉ አጽኖት ሰጥተዋል።
የትግራይ ህዝብ ከጦርነት አዙሪት በመውጣት ወደ ሰላምና ልማት የመሸጋገር አላማ እንዳለው አንስተው አሁን ላይ በተለይም በከተሞች በርካቶች የህወሃት ቡድን እየጎሰመ ያለውን ጦርነት በመሸሽ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ የሰላም እና የልማት አጀንዳዎችን ይዞ የመቀጠል ፍላጎት ያለው መሆኑን ያነሱት አቶ ገብረጊዮርጊስ ይህ እንዲሳካ መስራት አለብን ብለዋል።
የህወሃት ቡድን ከጦርነት ውጭ ሌላ አጀንዳ የሌለው በመሆኑ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መኖር "ምቾት የማይሰጠው" የጥፋት ስብስብ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቡድኑ አባላት ካለባቸው ተጠያቂነት ለማምለጥና የዘረፉትን የህዝብ ሀብት ለመደበቅ ጦርነትን የህልውና ጉዳይ አድርገው እየሰሩበት ይገኛሉ ብለዋል።
የፌዴራል መንግስት ለክልሉ ሰላምና ልማት እያደረገ ያለውን ጥረት በእንዲህ አይነት ጥፋት ምክንያት ውጤታማ መሆን አለመቻሉንም ገልጸው፤ በጋራ በመቆም ህዝቡ ሊታገላቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።