በፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎች እርካታ 98 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል - ኢዜአ አማርኛ
በፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎች እርካታ 98 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦የፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለፉት 10 ወራት የዜጎችን የአገልግሎት እርካታ 98 ነጥብ 7 ማድረሱን የአገልግሎቱ ዳይሬክተር ጄኔራል አንተነህ ማሞ ገለጹ።
አገልግሎቱ በተበታተነ መልኩ የሚሰጡ አሰራሮችን በአንድ ጣሪያ ስር በማምጣት እስካሁን ከ160 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠቱንም ጠቅሰዋል።
በማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያገኙ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ባጠረ ጊዜ ቀልጣፋ አገልግሎት በማግኘት ጉዳያቸውን በአግባቡ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተቋቋመው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተበታተነ መልኩ የሚሰጡ አገልገሎቶችን በአንድ ቦታ ማግኘት የሚያስችል አሰራር ነው።
የፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አንተነህ ማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው በአንድ ቦታ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አሰራር ነው።
አገልግሎቱ ከተጀመረ በ10 ወራት ውስጥ በርካታ ማዕከላትን በማቋቋም ለዜጎች ግልፅ፣ ቀልጣፋና እርካታን ያሳደገ አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህም ዜጎች በአንድ ቦታ፣ ባጠረ ጊዜና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደገፈ አሰራር አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህም በአገልግሎቱ የዜጎች እርካታ 98 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።
ወደ መሶብ ያልገቡ ተቋማት የአሠራሩ አካል እንዲሆኑና ለአገልግሎት ጥራት መሻሻል የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ለዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎችና ከተሞች አገልግሎቱን በጥራት ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
ዳይሬከተሩ አክለውም፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እየተሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
ንግድ ፍቃድ ለማውጣት ወደ ማዕከሉ የመጡት ተገልጋይ አደመ አየለ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል የነበረው የተጓተተ ንግድ ፍቃድ የማውጣት ሂደት በመቀረፉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በተቋማት መካከል የተቀናጀና የተቀላጠፈ አሠራር መዘርጋቱ እንግልትንና ምልልስን አስቀርቷል ነው ያሉት።
ለኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት የመጡት ቤተልሔም እንግዳ፥ በማዕከሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህብረተሰቡ እርካታን የሚፈጥር ውጤታማ አሠራር በመሆኑ ዜጎች የዚህ ዘመናዊ አሰራር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።