ቀጥታ፡

የገጠር መሬትን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር አርሶአደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው

አሶሳ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦ የገጠር መሬትን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር አርሶአደሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬትና ህብረት ስራ ማደራጃ ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ብሔራዊ መታወቂያ ለገጠር መሬት ባለይዞታዎች" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ትዕግስቱ ገብረመስቀል እንደገለፁት፤ የገጠር መሬትን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ዘላቂ የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና ብልሹ አሰራርን ማስቀረት ይቻላል።

አርሶ አደሩ ማሳውን አስይዞ የብድር አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ምርትና ምርታማነቱን  ለማሳደግ እንዲችልም የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉት ከ50 ሚሊዮን በላይ የአርሶ አደር ማሳዎች መካከል 32 ሚሊዮን ለሚሆኑት የባለቤትነት ይዞታ መሰራቱን ለአብነት አንስተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው፤ የገጠር መሬትን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የማስተሳሰሩ ሂደት አርሶ አደሩን በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።


 

ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመተግበር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር እንደሆነም አስረድተዋል።

ትግበራው የመሬት አስተዳደርን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲካሔድ በማድረግ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ሲሆን  መሬትን ለተፈለገው አገልግሎት ለመጠቀም ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

የክልሉ መሬትና ህብረት ሥራ ማደራጃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀሚድ  በበኩላቸው፤ ‎በክልሉ  ለ277 ሺህ 274 ማሳዎች ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሠጠቱን ነው የተናገሩት። 


 

‎አርሶ አደሩ የመሬት ባለቤትነት መብቱን በመጠቀም ማሳውን በማልማት፣ በማከራየት እንዲሁም ከባንክ ጋር በማስተሳሰር የብድር አቅርቦት ማግኘት እንደሚችል ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ የፌዴራል፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም