የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስኬቶች የከተሞችን ትንሳኤ በማብሰር ዘመናዊ የአኗኗር ምዕራፍ የከፈቱ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስኬቶች የከተሞችን ትንሳኤ በማብሰር ዘመናዊ የአኗኗር ምዕራፍ የከፈቱ ናቸው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስኬቶች የከተሞችን ትንሳኤ በማብሰር ዘመናዊ የአኗኗር ምዕራፍ የከፈቱ መሆናቸውን የምህንድስና ባለሙያዎች ገለጹ።
በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደርና ከተማ ዕድሳት የልማት ሥራ አሁን ላይ ተደራሽነቱን በማስፋት በርካታ ከተሞችን ውብ ገጽታ ማላበስ ያስቻለ እመርታዊ ስኬት እያስገኘ ነው።
የከተሞች የኮሪደርና ዕድሳት የልማት ሥራም ዘመናዊ ኢኮኖሚ፣ አስተዳደር፣ ከባቢ፣ እንቅስቃሴ፣ ነዋሪና የአኗኗር ሥርዓትን የሚያጎናጽፉ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎችን የተከተሉ ናቸው።
ለአብነትም በ2018 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሃያ አንድ የኢትዮጵያ ከተሞችን ለነዋሪዎችና ጎብኝዎቻቸው ምቹ ገጽታን ማላበስ የሚያስችል ዘመናዊ የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የምህንድስና ሙያተኞችም፤ የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደርና የዕድሳት የልማት ሥራ ታሪክን ከዘመናዊነት በማሰናሰል ምቹ የአኗኗር ዘይቤን ማጎናጸፍ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የስማርት ሲቲ ባለሙያ ዮዲት ገብረአሊፍ (ዶ/ር)፤ የኮሪደር ልማት ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባሻገር ዜጎችን ስልጣኔና ዘመናዊ አኗኗር የሚያጎናጽፍ ነው ብለዋል።
ለአብነትም አዲስ አበባን ውብ ገጽታ ያላበሷት የኮርደርና የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎቶች ለዘመናዊ ከተማ ግንባታ ትርጉም የሚሰጣቸው ወሳኝ የልማት መሠረቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ህንፃ መምህርና የከተማ ፕላን ባለሙያ መስፍን አለሙ፤ የኮሪደር ልማቱ ከተሞች በዘፈቀደ የሚመሩበትን ተለምዷዊ አሰራር በመቀየር ማራኪና ውብ ገጽታ ማላበስ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ከተሞች የኮርደር ልማት የተመዘገቡ አስደናቂ ለውጦች የከተሞችን ትንሳኤ በማብሰር ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን በመፍጠር አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ ናቸው ብለዋል።
የኮሪደርና ከተማ ዕድሳቱም ነዋሪዎችና ጎብኝዎች ጤናማ የእንቅስቃሴ ሥርዓት እንዲጎናጸፉ በማስቻል ለከተሜነት ግንባታ ትርጉም የሚሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ዘመናዊ የከተማ ልማት ተግባራትም ዜጎችን ከሚያጎናጽፋቸው ዘመናዊ አኗኗር ሥርዓት ባሻገር የተቋማትን አገልግሎቶች በማዘመን የአገልግሎት እርካታን መፍጠር እንደሚያስችሉ ሙያተኞቹ አንስተዋል።
ኢትዮጵያዊያንም የከተሞችን ማራኪ የልማት ሥራዎች በባለቤትነት በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ከተሞችን ዘመናዊ ገጽታ የማላበስ ተግባር በማስቀጠል በዕውቀትና ክህሎት የሚመሩና ጤናማ ዕድገትና አገልግሎት የሚከተሉ ከተሞችን መገንባት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።