ቀጥታ፡

የማር ልማት ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ መደረጉ ተጨማሪ ገቢ እንድናገኝ አስችሎናል - አርሶ አደሮች

ሮቤ ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦የማር ልማት ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ መደረጉ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ በባሌ ዞን የሐረና ቡሉቅና ደሎ መና ወረዳ አርሶና አርብቶ አደሮች ገለጹ። 

በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ለማር ልማት ኢኒሼቲቭ በተሰጠው ትኩረት ከ8 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት መገኘቱን  የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ባሌ ዞን ማር በስፋት ይመረታል።

የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ አድርጎናል

ይሕንኑ መነሻ በማድረግም ጥራቱን የጠበቀ የማር ምርት ለገበያ ለማቅረብ በተከናወኑት ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እየታየ መጥቷል።

በዞኑ ሐረና ቡሉቅና ደሎ መና ወረዳ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአካባቢው ተግባራዊ የተደረገው የማር ልማት ኢኒሼቲቭ ምርታማነትን ያሳደገ በመሆኑ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት አስችሎናል ብለዋል።

አርሶ አደር ሁሴን አህመድ እንዳሉት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በመጠቀምና የተሻሻሉ አሰራሮችን በመተግበር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸዋል።


 

በዚህም ከአንድ ባህላዊ ቀፎ  ይገኝ የነበረውን 7 ኪሎ ግራም ማር ወደ 20 ኪሎ ግራም ለማሳደግ  ከመቻሉ ባለፈ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት የተሻለ ኑሮ ለመምራት አስችሎኛል ነው ያሉት።

መንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ በሚያቀርበው  ዘመናዊ ቀፎ መጠቀም በመቻላቸው  የማር ምርታቸውን ለማሳደግ እንደቻሉ የሚገልጹት ደግሞ በደሎ መና ወረዳ በንብ ማነብ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ አብዶ ከድር ናቸው።


 

ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ለንብ ማነብ ስራ እድገትና መስፋፋት አመቺ ሁኔታዎችን እንደፈጠረላቸውም ነው ያመለከቱት።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታቸው አበባ በበኩላቸው፤ የማር ምርት ኢኒሼቲቭ በዞኑ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ እያስቻለ መጥቷል ብለዋል።


 

ኢኒሼቲቩ ከመጀመሩ በፊት የዞኑ ዓመታዊ የማር ምርት ከ2 ሺህ ቶን የማይበልጥ ነበር ያሉት ኃላፊው ኢኒሼቲቩ ተግባራዊ በመደረጉ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ8 ሺህ ቶን በላይ ማር ማምረት እንደተቻለ ተናግረዋል።

በዞኑ የነበረውን ከ20 ሺህ የማይበልጥ የዘመናዊ ቀፎ ብዛት በአሁኑ ወቅት ከ85 ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉንም አንስተዋል።

በመስኩ እየታየ ያለው ውጤትም ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሩ በስፋት ከማቅረብ ባሻገር በዘርፉ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር በመቻሉ እንደሆነም አስረድተዋል።

ኢኒሼቲቩ የዘርፉን ምርታማነት ከማሳደግ ባሻገር 2 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም