አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት እመርታ ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት እመርታ ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦ አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ በሀገሪቱ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ላይ ከፍተኛ እመርታ መመዝገቡን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የተገኘውን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል።
የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል
ግብርና ሚኒስቴር ሀገር አቀፍ የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ኤክስቴንሽን የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የእንስሳት ልማት ትልቅ እመርታ አሳይቷል።
አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር በእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ላይ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
የእንስሳት ሀብት ልማት ቀደም ሲል በስትራቴጂ ደረጃ ተዘንግቶ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ግን ራሱን ችሎ እንዲደራጅና ትኩረት እንዲሰጠው መደረጉን አንስተዋል።
የኤክስቴንሽን ሥርዓትን በመተግበር በእንስሳት ጤናና ምርታማነት ላይ እውቀትንና ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅና እንዲጠቀም በማድረግ ለውጥ መምጣቱንም ገልፀዋል።
አርሶ እና አርብቶ አደሮች በባለሙያ የታገዘ የእንስሳት በሽታን በመከላከል ረገድ ውጤታማ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በምርምር የተገኙ ቴክኖሎጂዎችን፣ የዝርያ ማሻሻያ ሥራዎችንና የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ዘዴዎችን ተግባር ላይ ለማዋል ሰፊ ክፍተት ቢኖርም፣ የተጀመሩት ሥራዎች ተስፋ ሰጭ እንደሆኑ አስረድተዋል።
የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ ለማጠናከር የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።