በሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ሪያል ማድሪድ ከቤኔፊካ ፒኤስጂ ከሞናኮ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ሪያል ማድሪድ ከቤኔፊካ ፒኤስጂ ከሞናኮ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ መርሐ-ግብር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
በበርናባው ስታዲየም ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ሪያል ማድሪድ ከቤኔፊካ ይጫወታሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር በስታዲዮ ደሉዝ ባደረጉት ጨዋታ ሪያል ማድሪድ በቪኒሺየስ ጁኒየር ጎል 1 ለ 0 አሸንፏል።
የ15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ወደ ጥሎ ማለፉ ያስገባዋል።
ቤኔፊካ ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል ከሁለት እና ከዚያ በላይ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የወቅቱ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ፒኤስጂ ከሞናኮ ምሽት አምስት ላይ በፓርክ ደ ፕሪንስ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሁለቱ የፈረንሳይ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ፒኤስጂ 3 ለ 2 አሸንፏል።
ፒኤስጂ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ወደ ጥሎ ማለፉ ይገባል። ሞናኮ ከሁለት እና ከዚያ በላይ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ጥሎ ማለፉን ይቀላቀላል።
ምሽት አምስት ላይ ጁቬንቱስ ከጋላታሳራይ በአሊያንዝ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
በመጀመሪያው ዙር የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጋላታሳራይ 5 ለ 2 አሸንፏል። የቱርኪዬው ክለብ ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድሉ ሰፊ ነው።
የጣልያኑ ክለብ ጁቬንቱስ ለማለፍ ከአራት እና ከዚያ በላይ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይኖርበታል። ይህም ፈተናውን የበለጠ ያከብድበታል።
አትላንታ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ በቤርጋሞ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር በሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የማለፍ እድሉ ሰፊ የሆነው ዶርትሙንድ ማሸነፍ፣ አቻ መውጣት እና በአንድ የግብ ልዩነት መሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ያስገባዋል።
የጣልያኑ አትላንታ ውጤቱን ቀልብሶ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ከሁለት እና ከዚያ በላይ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
ትናንት በተደረጉ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታዎች ኒውካስትል ዩናይትድ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ባየር ሌቨርኩሰን እና ቦዶ ግሊምት ተጋጣሚዎቻቸውን በድምር ውጤት በማሸነፍ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅለዋል።