የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ ልደታ ክፍለ ከተማ ከይርጋጨፌ ቡና በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ልደታ ክፍለ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ 10 ጊዜ ተሸንፏል። በሁለቱ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
በ14ቱ ጨዋታዎች ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 27 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በስምንት ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ይርጋጨፌ ቡና በበኩሉ በውድድር ዓመቱ 14 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው በሰባቱ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ስድስት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 18 ግቦች ተቆጥረውበታል። ይርጋጨፌ ቡና በ11 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለተቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
በሌላኛው መርሐ- ግብር አርባምንጭ ከተማ ከከቦሌ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 14 ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ዘጠኝ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በ14ቱ ጨዋታዎች ላይ 10 ግቦችን ሲያሳርፍ 26 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በዘጠኝ ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በሊጉ 14 ጨዋታዎችን አድርጎ በስድስቱ አሸንፎ በሶስቱ ተሸንፎ በአምስቱ አቻ ወጥቷል። 15 ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ጎሎች ገብተውበታል።
ቡድኑ በ23 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ጨዋታው አርባምንጭ ከተማ ወደ ድል ለመመለስ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዘገብ የሚያደርጉት ነው።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት እስከ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ37 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ18 ግቦች እየመራች ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በ12 ጎሎች ትከተላለች።