ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮ-እስራኤል ታሪካዊ ትስስር - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮ-እስራኤል ታሪካዊ ትስስር
(በአየለ ያረጋል)
ጥልቅ ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር ያላቸው ሀገራት ናቸው፤ ኢትዮጵያና እስራኤል። የሁለቱ ሃገራት ዘመናትን የተሻገረው ግንኙነት አሁን ላይ በተለያዩ መስኮች የተጠናከረ ሆኖ ይገኛል። የሀገራቱ ግንኙነት ግን እንደየስርዓተ መንግስታቱ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ባህሪ መልኩን እየለዋወጠ እና ውጣ ውረዶችን እያለፈ የተሻገረና ጠንካራ መሆኑም ይታወቃል።
የእስራኤል ፕሬዝዳንት ኢሳክ ሄርዞግ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሃገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጠቅሰው የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ፕሬዝዳንቱ ወደ አዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን(ዶ/ር) ጨምሮ ከተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩም ይጠበቃል።
ኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት ታሪካዊ ገጽታ፦
ሃገራቱ የግንኙነታቸው ትርክት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በንግሥተ ሳባ እና በንጉሥ ሰለሞን ዘመነ መንግስት እንደሆነ አፈ ታሪክ ያስረዳል። ይህ አፈ-ታሪካዊ እርሾ ከኢትዮጵያ ሰለሞናዊ ስርወ መንግስት ጋርም ቀጥሏል። በመካከለኛው እና በዘመነ መሳፍንት ዘመን ሃይማኖትና ንግድ ሁለቱን ሀገራት ይበልጥ አስተሳስሯል። በተለይም ዴር ሱልጣንን ጨምሮ በኢየሩሳሌም የሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማት መኖር የሁለቱን ሀገራት ባህላዊ ተጋምዶሽ አጎልብቷል። ይህ ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር ከእስራኤል ሀገረ መንግስት ዳግም መመስረት በኋላም በዘመናዊት ኢትዮጰያ ታሪክም ቀጥሏል።
የኢትዮ እስራኤል ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ፦
የዘመናዊ የኢትዮ-እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት የተወጠነው በአውሮፓዊያኑ ዘመን ቀመር በ1956 ሲሆን በ1961 ይፋዊ የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጀምሯል። በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግስት የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት ይፋዊ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ስትራቴጂካዊ ጥቅምን ያማከለና የወቅቱን የቀጣናውን ነባራዊ ሁኔታ የዋጀ ግንኙነት እንዲመሰርቱ አድርጓል። በንጉሳዊ ስርዓተ መንግስት ሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ እና ሌሎች የልማት ቴክኒካል ድጋፍ የደረሰ ወዳጅነት ነበራቸው።
በደርግ ዘመነ መንግስት ሁለቱ ሀገራት በእስራኤለና አረቦች ጦርነት ሳቢያ መቀዛቀዝ ተስተውሎበታል። ያም ሆኖ በግልጽም ሆነ የህቡዕ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደነበራቸው ይወሳል። መጀመሪያ ላይ ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት በደርግ መንግስት መጨረሻ ዓመታት (በአውሮፓዊያኑ 1989) የኢትዮ-እስራኤል ይፋዊ ግንኙነት ዳግም ተጀምሯል። የ"ኦፕሬሽን ሙሴ" (1984) እና "ኦፕሬሽን ሰለሞን" (1991) የተሰኙ ቤተ እስራኤላዊያን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤለ የሟጓጓዝ ተልዕኮዎችም በሁለቱ ሀገራት መንግስታት ስምምነት የተካሄዱ መሆናቸውን ልብ ይሏል።
በኢህአዴግ ዘመን መንግስት (ከ1983 ዓ.ም) ጀምሮ ደግሞ የሀገራቱ ግንኙነት ወደ ተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቀጥሏል። በፈረንጆቹ 1992 ኢትዮጵያ በእስራኤል ኤምባሲዋን ከፍታለች። በፈረንጆቹ 2003 ኢትዮጵያና እስራኤል የኢንቨስትመቶች ማስፋፊያና ጥበቃ ስምምነት ተፈራርመዋል። በ1996 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 2004) የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በእስራኤል ጉብኝት አድርገዋል። ከወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሻሮን ጋር ያደረጉት ታሪካዊ ውይይት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አሳድጎታል ። ጉብኝቱን ተከትሎ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ያጠናከሩ የተለያዩ ስምምነቶች ተደርገዋል። በተለይም በቴክኖሎጂና ግብርና ዘርፍ የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ የልማት ትብብር ከፍ ብሏል። በአፍሪካ ቀንድ ደህንነትና ፀረ ሽብር ጉዳዮች እንዲሁም በወታደራዊ ስልጠና፣ የደህንነት መረጃ ልውውጥና የድንበር ጥበቃ ቴክኖሎጂ በትብብር ለመስራት መሰረት ጥለዋል።
በአውሮፓዊያን አቆጣጠር 2016 ደግሞ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በአዲስ አበባ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል። ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋርም መክረዋል። በተመሳሳይ በፈረንጆቹ በ2017 የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ እስራኤልን ጎብኝተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት በየራሳቸው ብሔራዊ ጥቅሞች ዙሪያ በትብብር ቆመዋል። በዓለም አቀፍ መድረኮች አንዳቸው ለሌላው ድምጽ በመስጠት ተደጋግፈዋል። የባሕር በር ባለቤትነትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ለብሔረታዊ ጥቅሞቿ መጠበቅ ለምታደርገው ጥረት እስራኤል አሉታዊ ምላሽ አልሰጠችም። ይልቁንም እስራኤል ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ እንደ መግቢያ ሁነኛ በር አድርጋ ትቆጥራለች።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮ-አስራኤል ግንኙነት ወደላቀ ስትራቴካዊ አጋርነት አድጓል። በ2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በእስራኤል ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ደግሞ የሀገራቱ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአዲስ ምዕራፍ እንዲታደስ አስችሏል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ታሪካዊ የተሰኘውን ምክክር አድረገዋል።
መሪዎቹ በሰጡት ገለጻም በአምስት ነጥቦች ላይ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶችን በኢኮኖሚ፣ በግብርና፣ በውሃ፣ በመስኖ፣ በጤና እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ መፈራረማቸውን አውስተው ነበር። በግብርና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በጸጥታ ዘርፎች ላይ አብሮ ለመስራት ተስማምተው እንደነበርም እንዲሁ።
ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ፦
ሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ትስስራቸውን ወደ ልማት በመለወጥ የንግድና ኢንቨስመንት ግንኙነታቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አከናውነዋል። የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እየጎለበተ መጥቷል። ለአብነትም የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በዘመናዊ ግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ተሰማርተዋል። በማዕድን ዘርፍ (በፖታሽ)፣ በማምረቻ ዘርፍ( በጨርቃጨርቅ እና በኬሚካል ኢንዱስትሪዎች) እንዲሁም በጤናና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወኑ ነው። በተለይም በግሪን ሃውስ፣ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ፣ በማምረቻ እና በፋርማሲዩቲካል (የመድኃኒት) ዘርፎች ሁነኛ ተሳትፎ አድርገዋል።
በተመሳሳይ በንግድ ልውውጥ ረገድ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሰሊጥና ሌሎች የቅባትና የጥራጥሬ ምርቶችን ወደ እስራኤል በስፋት ትልካለች። በአንጻሩ እስራኤል የላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ የግብርና ግብዓቶችን (ማዳበሪያና ኬሚካሎች)፣ የሕክምና መሣሪያዎችን እና የደህንነት ቁሳቁሶችን ለኢትዮጵያ ታቀርባለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ በደረቅ አካባቢ ግብርና ስመጥር የሆነችው እስራኤል በዘርፉ የኢትዮጵያ ቀዳሚ የልማት አጋር ስትሆን በዘመናዊ መስኖ፣ የአቮካዶና የፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በእንስሳት እርባታ እና የወተት ምርታማነት አጋዥ ቴክኖሎጂዎች በጎ ተሳትፎ ታደርጋለች።
በሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ወዳጅነት መጠናከር ቤተ-እስራኤላውያን እንደ ድልድይ አገልግለዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ160 ሺህ በላይ መሰረታቸው ከኢትዮጵያ የሆኑ እስራኤላዊያን ዜጎች አሉ። እነዚህ ዜጎች ለኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ሁነኛ ድልድይ ሆነዋል። በተለይም በእስራኤል የሰለጠኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በማስቻል በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እና በንግድ ስራ ረገድ ውጤታማ ግንኙነት እንዲፈጠር መልካም አጋጣሚ ፈጥጠሯል። ይህም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያቸውን ከፍ አድርጎታል።
የፕሬዝዳንት ሔርዞግ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ መምጣት የሁለቱን ሃገራት የጸና ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ የሚያጎለብት እንደሚሆን ይጠበቃል። በአህጉራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይም በጋራ የሚያከናውኑትን ስራ የሚያጠናክሩበት ምቹ ሁኔታም ይፈጥራል።