የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክሮችና የምረጡኝ ቅስቀሳዎች በመፍትሄ አማራጮች ላይ ያተኮሩ ሊሆኑ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክሮችና የምረጡኝ ቅስቀሳዎች በመፍትሄ አማራጮች ላይ ያተኮሩ ሊሆኑ ይገባል
ወላይታ/አዳማ/ድሬዳዋ/ሆሳዕና፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረኮችና የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ቅራኔና ግጭት ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ ንግግሮች በመራቅ የመፍትሄ አማራጮች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ በተለያዩ ከተሞች ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን የምርጫ ምልክት ይፋ ባደረገበት መድረክ ፓርቲዎቹ የምርጫ ስነ-ምግባር ደንብ መፈረማቸው ይታወቃል።
ጠቅላላ ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲካሄድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግን አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ቦርዱ አስገንዝቧል።
በምርጫ ቅስቀሳም ሆነ በክርክር መድረኮች የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በፈረሙት የስነ-ምግባር ደንብ መሰረት ፕሮግራማቸውን ሊያስተዋውቁ እንደሚገባና የህዝብ መገናኛ ብዙሃንም ለሁሉም እኩል ዕድል ሊሰጡ እንደሚገባ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አከራካሪ የሆኑ ምርጫ ክልሎችን በተመለከተ ውሣኔ አስተላለፈ
በዚህም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን በማስመዝገብ በምርጫው ብቁ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ በተለያዩ ሚዲያዎች የምርጫ ክርክሮችን ማድረግ ጀምረዋል።
በክርክሮቹ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ለሀገርና ህዝብ ይጠቅማሉ የተባሉ ሃሳቦች በመቅረብ ላይ ይገኛሉ።
በመሆኑም አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱንና የእስካሁኑን የፓርቲዎች እንቅስቃሴ በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተሮች የወላይታ ሶዶ፣ የአዳማ፣ የድሬዳዋ እና የሆሳዕና ከተሞች ነዋሪዎችን አነጋግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች እራሳቸውን በማስተዋወቅ የፖሊሲና የሃሳብ ክርክሮች መጀመራቸው ለመራጩ ውሳኔ ወሳኝ ግብአት መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የፓርቲዎች የክርክር መድረኮችና የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ቅራኔና ግጭት ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ ንግግሮች በመራቅ የመፍትሄ አማራጮች ላይ እንዲያተኩሩ ገልጸዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪው ሺመልስ ተፈራ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ሲያስተዋውቁና የምርጫ ክርክር ሲያደርጉ እየተከታተልን እንገኛለን ብለዋል።
በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ፕሮግራማቸውን ሲያስተዋውቁ ቢመረጡ በቀጣይ ምን ሊተገብሩ እንዳሰቡ ለማወቅ እያስቻለ ስለመሆኑ አንስተው፤ በክርክሩ የፖለቲካ ባህል እያደገ መምጣቱን ያየንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም ለሀገርና ህዝብ የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሚያኖር ተግባር ፈፅመው የማለፍ አደራ አለባቸው ብለዋል።
የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ዋቅጋሪ ቢራቱ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠቅላላ ምርጫው በሃሳብ የበላይነት፤ ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ጉዳዮችን በመያዝ በአጀንዳዎች ላይ ክርክር ማድረጋቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በዚህም ሀገረ መንግስትን ማስቀጠል የሚያስችሉ ጠቃሚና ገንቢ ሃሳቦች እንደሚገኙበት አምናለሁ ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪ የሆኑት ደረጄ ጉተማ በበኩላቸው በምርጫ ክርክር ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገርን ትልቅ የሚያደርጉ ሀሳቦች ላይ አተኩረው መስራት እንዳለባቸው አንስተዋል።
ሀገርን የሚገነባ ሀሳብ የሚያራምድ ፓርቲ ለህዝብ የሚጠቅምና ለሀገር ግንባታ ሁነኛ መሰረት የሚያኖር መሆኑንም አንስተዋል።
በጠቅላላው ምርጫው በሀሳብ የበላይነት ለመወዳደር ወደ ሜዳ የሚገቡ ፓርቲዎች ሀገርን ሊያሻግር የሚችል ሃሳብ ይዘው ሊመጡ ይገባል ያሉት ደግሞ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪው ከበደ ኦሴቦ ናቸው።
የክርክር መድረኩ ለፖለቲካ ፓርቲዎች አንዲት የጋራ ሀገር ለመምራት የሚያደርጉት ጥረት በመሆኑ ለሀገር የሚበጁ ሃሳቦችን በመሰነቅ መንቀሳቀስ እንዳሚገባቸው ተናግረዋል።