ቀጥታ፡

ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የተቀናጀ አሰራርን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ  ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያዘጋጀው 4ኛው አገር አቀፍ የፀረ ህገ-ወጥ ንግድ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።  


 

በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አዘዘው ጫኔ እንደገለጹት፤ ህገ-ወጥ ንግድ በነጋዴው፣ በህብረተሰቡና በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ያደርሳል፡፡

መንግሥት አገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ ሕገ-ወጥ ንግድን ለመግታት አሠራርን የማሻሻል፣ ቴክኖሎጂን የመጠቀምና ሌሎች በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል። 

በዚህም ህገ-ወጥነትን የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አመልክተዋል።

ሆኖም የህገ-ወጥ ንግድ ባህሪ ተለዋዋጭ በመሆኑ አሁንም በመከላከል ረገድ ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተለይም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ የጋራ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ንግድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሊቁ በየነ በበኩላቸው፤ ህገ-ወጥነት በሸማቹና በነጋዴው መካከል ያለውን ፍትሀዊ ውድድር የሚያናጋ ትልቅ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል። 

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ለመቅረፍ አሠራሩን በዘመናዊ መንገድ እያደራጀ መሆኑን ጠቅሰው በንግድ ሥርዓቱ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አይናለም አባይነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ የንግዱን ማህበረሰብ ግንዛቤ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በቀጣይም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም