ኢትዮጵያ 16ኛውን የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ጠቅላላ ጉባኤን ለማዘጋጀት ተመረጠች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ 16ኛውን የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ጠቅላላ ጉባኤን ለማዘጋጀት ተመረጠች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ 16ኛውን የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ጠቅላላ ጉባኤን ለማዘጋጀት መመረጧን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ 16ኛውን የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ጠቅላላ ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል።
የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ትስስር በአህጉሪቱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን የማስተባበር፣ አቅም የመገንባትና እርስ በርስ በማቀናጀት የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚሰራ ነው።
ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ትስስር 16ኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ውሳኔ የተላለፈው በየካቲት ወር 2026 በካሜሩን ያውንዴ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው።
ኢትዮጵያ 16ኛውን የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ጠቅላላ ጉባኤን ለማዘጋጀት መመረጧ በሀገሪቷ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ለተከናወኑ ተግባራት እውቅና የሰጠ ነው ብለዋል።
ጉባዔውም ኮሚሽኑ ቀጣይ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ከአቻ ተቋማት ጋር ልምድና ተሞክሮ የሚጋራበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ጉባዔውን ለማስተናገድ የሚያስችል እቅድ አውጥቶ ወደስራ መግባቱን የገለፁት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ለጉባዔው መሳካት የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በታራሚዎች አያያዝ፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ፣ የአካል ጉዳተኞች የተጠቃለለ ሕግ ማውጣት የሚያስችል ፖሊሲ ዝግጅትና በማህበረሰብ ድርጅቶች ምኅዳር ላይ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች አያያዝ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መሻሻል እንደሚታይባቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የማሻሻያ ሥራዎች ማከናወኑንም አስረድተዋል።
ጉባዔው በ2019 ዓ.ም እንደሚካሄድም ነው ዋና ኮሚሽነሩ የገለጹት።