የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እና ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አምራቾች ገለጹ፡፡
ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተማ አቀፍ ባዛርና ኤግዚቢሽን “ኢትዮጵያ ታምርት፤ አዲስ አበባ ትበልፅግ” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መከፈቱ ይታወሳል።
የመንግስት የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው ዕድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ነው
ለአንድ ሳምንት በሚቆየው በዚህ መድረክ ላይ የጨርቃጨርቅ፣ የሕክምና፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ለዕይታ ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ዘርፉን በማነቃቃት፣ የውጭ ምንዛሬን በማዳንና አዳዲስ የገበያ ትስስሮችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አምራቾችም፤ ንቅናቄው ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
የቲ ማክስ ኤሌክትሮኒክስ ተወካይ ሳሊ መሐመድ፤ ድርጅቱ ቀደም ሲል ያለቀላቸውን የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ከውጭ በማስገባት ላይ ተሰማርቶ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ ግን ትኩረቱን ወደ ሀገር ውስጥ ምርት ማዞሩን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ፓወር ባንኮችን፣ ቻርጀሮችን፣ ፍላሾችን፣ የማከፋፈያ ገመዶችንና የሞባይል ባትሪዎችን በማምረት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህ ስኬትም ከወረዳ፣ ከክፍለ ከተማና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚደረገው ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
የጣና የቆዳና ጨርቃ ጨርቅ ስራ አስኪያጅ አቶ አብይ አበበ፤ ድርጅታቸው በገበያ ላይ ተፈላጊ የሆኑ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ግብዓት እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል።
ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አዳዲስ የገበያ ትስስሮችን ለመፍጠር እንደረዳቸው አስረድተዋል።
የዶሪ ኢንጂነሪንግ ተወካይ አቶ ምስጋናው ወልደሰንበት፤ ድርጅታቸው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ የነበሩ መለዋወጫዎችን በሀገር ውስጥ እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ ለቴሌኮም እና ለባቡር መሰረተ ልማት የሚሆኑ ግብዓቶችን እንዲሁም የተለያዩ የማሽንና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን በማምረት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ምርቶቻቸውን ለአዲስ አበባና ለተለያዩ ክልሎች እያቀረቡ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በቀጣይ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።