ቀጥታ፡

የኢትዮ-ቱኒዚያን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ወደላቀ ኢኮኖሚያዊ የትብብር ምዕራፍ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ቱኒዚያን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ወደላቀ ኢኮኖሚያዊ የትብብር ምዕራፍ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን የቱኒዚያ የውጭ፣ ስደተኞችና የዳያስፖራ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ አሊ ናፍቲ ገለጹ። 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሚኒስትሩ፥ በኢትዮጵያና ቱኒዚያ መካከል የረጅም ዘመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መኖሩን ገልጸዋል።

በተለይም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ በትብብር የሚሰሩ ወዳጅ ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በንግድና ኢኮኖሚ የትብብር መስክ  የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ወደላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር እየሰሩ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በዚህም ቱኒዚያ በግብርና፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቱኒዚያ መዲና ቱኒስ የሚያደርገው የቀጥታ በረራ አገልግሎት የሁለቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር የንግድ ሸቀጦችን ዝውውር በማቀላጠፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያና ቱኒዚያን የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከርም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና ማዕቀፍ መሠረት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስማማታቸውን አስታውሰዋል።

በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሚያደርጉት ውይይት በሰላምና ደኅንነት እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የጋራ አቋም እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ በማሳደግ ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነትና አህጉራዊ ተጽዕኖ በጠንካራ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንደሚያስቀጥሉ አንስተዋል።

ከ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን የተደረጉ ውይይቶች የሀገራቱን የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ለማጠናከር የሚያስችሉ እንደሆኑም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አስደናቂ ሁለንተናዊ ሪፎርም እርምጃ ወስዷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የአፍሪካን ዘላቂ የጋራ ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ መሪ ሃሳብ በውሃ ሃብት ላይ ያተኮረ መሆኑ የሕብረቱን አጀንዳዎች ዕውን ለማድረግ አቅም ይፈጥራልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም